ትምህርት ሚኒስቴር የዩንቨርሲቲ መግቢያ ፈተና ተፈታኝ ተማሪዎች ቅሬታን ተቀብሎ እንዲፈታ የሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም አሳሰበ
ትምህርት ሚኒስቴር እና ሀገር አቀፍ ፈተናዎች ኤጀንሲ የተፈታኝ ተማሪዎችን ቅሬታ እያስተናገዱ አለመሆኑንም ተቋሙ ገልጿል
በጦርነት ውስጥ ሆነው የተፈተኑ ተማሪዎች በልዩ ሁኔታ ድጋፍ ይደረግልን በሚል ለቀረበው ጥያቄ ሚኒስቴሩ ተገቢ መልስ እንዲሰጥም ተቋሙ ጠይቋል
ትምህርት ሚኒስቴር የዩንቨርሲቲ መግቢያ ፈተና ተፈታኝ ተማሪዎች ቅሬታን ተቀብሎ እንዲፈታ የሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም አሳሰበ።
የኢትዮጵያ ህዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም የ2013 ዓ.ም የ12ኛ ክፍል የዩንቨርሲቲ መግቢያ ፈተናን አስመልክቶ ከተፈታኝ ተማሪዎች ቅሬታ እንደቀረበለት ገልጿል።
ተቋሙ በ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ የዩኒቨርሲቲ መግቢያ ፈተናን አስመልክቶ ለተቋሙ የቀረቡ ጥቆማዎች እና በተለያዩ ሚዲያዎች ጉዳዩን አስመልክቶ የቀረቡ ዘገባዎችን መነሻ በማድረግ ጉዳዩን መርምሬያለሁ ብሏል።
በተደረገው ምርመራ መሰረትም የፈተናዎች ኤጀንሲ የፈተና እርማትን አስመልክቶ ተማሪዎች ያቀረቡትን ቅሬታ በመቀበል ምላሽ መስጠቱን የገለጸ ቢሆንም የተቋሙ መርመሪዎች ለምርመራ ስራ በኤጀንሲው በተገኙበት ወቅት በርካታ ተማሪዎች ቅሬታቸውን ለማቅረብ በኤጀንሲው ቢገኙም ወደ ውስጥ ገብቶ ቅሬታን ለማቅረብም ሆነ ቅሬታቸውን ተቀብሎ ሊያስተናግዳቸው አልቻለም ተብሏል።
ከዚህ በተጨማሪም ተፈታኞቹ ቅሬታቸውን ለትምህርት ሚኒስቴር እንዲያቀርቡ ተነግሯቸዋል ያለው ተቋሙ ተፈታኞቹ ቅሬታቸውን ይዘው ወደ ትምህርት ሚኒስቴር በመሄድ ለማቅረብ ጥረት ቢያደርጉም በትምህርት ሚኒስቴር በኩል ጉዳዩ የሚመለከተው የፈተናዎች ኤጀንሲ ነው በሚል ቅሬታቸውን ሳይቀበል ቀርቷልም ብሏል።
በዚህ ምክንያትም ተማሪዎች እና ቤተሰቦቻቸው ከተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ቅሬታቸውን ለማቅረብ መጥተው ለእንግልት እየተዳረጉ እንደሚገኙ የተቋሙ መርማሪዎች በቦታው በመገኘት አረጋግጠዋል።
ማንኛውም ዜጋ በመንግስት ተቋማት አገልግሎት አሰጣጥ ላይ ያለውን ቅሬታ ለሚመለከተው አገልግሎት ሰጪ ተቋም የማቅረብ መብት እንዳለውና ቅሬታ የቀረበለት አካልም ቅሬታውን ተቀብሎ ያለምንም ገደብ ምላሽ የመስጠት ግዴታ እንዳለበት የህዝብ እንባ ተቋም አስታውቋል።
ይሁን እንጂ የፈተናዎች ኤጀንሲ እና ትምህርት ሚኒስቴር በአዋጅ የተጣለባቸውን ሀላፊነት ከመወጣት ይልቅ ቅሬታዎችን አጣርተን ጨርሰናል እና ጉዳዩ እኛን አይመለከትም በሚሉ ተገቢ ባልሆኑ ምክንያቶች የተማሪዎችን ቅሬታ ለመቀበል ፍቃደኛ አለመሆናቸውን እና ህግ መጣሳቸውን ተቋሙ ገልጿል።
የሀገር አቀፍ የፈተናዎች ኤጀንሲ በኦንላየን ለቀረቡለት ከ20 ሺህ በላይ ቅሬታዎች ምላሽ የሰጠ ቢልንም ለእነዚህ አቤቱታዎች የተሰጠው ምላሽ እንደቀረበው ቅሬታ አይነት በመለየት ሳይሆን ለሁሉም ቅሬታዎች ተመሳሳይ ምላሽ ማለትም ቅሬታው የታየ መሆኑን ብቻ የሚገልጽ ምላሽ መሆኑ ትክክል አለመሆኑንም የህዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም በምርመራ ግኝቴ አረጋግጫለሁ ብሏል።
በሁለት ዙር በተሰጠው የ2013 ዓ/ም የዩኒቨርሲቲ መግቢያ ፈተና በተለይ የሁለተኛ ዙር ፈተና እርማት ላይ ስህተቶች የተፈጠሩ መሆኑን የሀገር አቀፍ ፈተናዎች ኤጀንሲ በምርመራ ሂደት ወቅት ለተቋሙ መርማሪዎች አረጋግጧልም ብሏል።
በተጨባጭም የእርማት ስህተት አለ በሚል ቅሬታ ካቀረቡ ተፈታኝ ተማሪዎች መካካል ድጋሚ እርማት በተደረገ ወቅት ስህተት የተፈጠረ መሆኑን ማሳያ ወይም ማረጋገጫ መሆን የሚችሉ የማስተካካያ እርማቶች እና ውጤቶች መከሰታቸው በእርማት ሂደቱ ላይ ችግሮች መፈጠራቸውን የሚያረጋግጡ ማስረጃዎች መሆናቸውን ተቋሙ አረጋግጧል።
ፈተናው በሚሰጥበት ወቅት የጦርነት እና የጸጥታ ችግሮች በነበረባቸው አካባቢዎች ፈተናውን የወሰድን ተማሪዎች በልዩ ሁኔታ የዩኒቨርሲቲ መግቢያ ነጥብ ሊወሰንልን ይገባል በሚል የቀረበውን ጥቆማ በሚመለከት የትምህርት ሚኒስቴር ጉዳዩን አስመልክቶ የሰጠው ምላሽ ከመልካም አስተዳደር መርሆች አኳያ ተገቢ ውሳኔ አለመሆኑን የህዝብ እንባ ተቋም ገልጿል።
በመሆኑም ሀገር አቀፍ የፈተናዎች ኤጀንሲ የፈተና እርማትን አስመልክቶ ከሁሉም የሀገሪቱ አካባቢዎች ከተፈታኝ ተማሪዎች እና ወላጆች የሚቀርቡ አቤቱታዎችን ተገቢውን ጊዜ ሰጥቶ ያለምንም ገደብ በአካል፣ ኦንላይን የአቤቱታ ማቅረቢያ ጨምሮ ሁሉንም አማራጮች ተጠቅሞ አቤቱታዎች በመቀበል ተገቢውን የሰው ሀይል በመመደብ ለቅሬታዎቹ ግልጽ እና ምክንያታዊ ምላሽ እንዲሰጥ ተቋሙ አሳስቧል።
በተለይ በኦን ላይን ለቀረቡ አቤቱታዎች እየተሰጡ ያሉ ምላሾች በአግባቡ የታዩ እና ማጣራት የተደረገባቸው ስለመሆናቸው ተገቢው ቁጥጥር እንዲደረግባቸውም ተቋሙ ጠይቋል።
እንዲሁም በ2013 ዓ/ም የትምህርት ዘመን በሁለተኛ ዙር የዩኒቨርሲቲ መግቢያ ፈተና የወሰዱ ተማሪዎች የፈተና እርማት ሂደት ላይ ስህተቶች መፈጠራቸው የተረጋገጠ በመሆኑ በሁለተኛው ዙር እርማት ተጨማሪ ስህተት አለመኖሩን ድርጅቱ በሚያረጋግጥበት ስርአት አረጋግጦ ለአቤት ባዮች አጥጋቢ ምላሽ እንዲሰጥም የህዝብ እንባ ቷም አሳስቧል።
ከዚህ በተጨማሪም የትምህርት ሚንስቴር በጦርነት ወይም የጸጥታ ችግር በነበረባቸው አካባቢዎች የተመዘገበውን የተማሪዎች ዉጤት በአንጻራዊነት ሰላም በነበረባቸው አካባቢዎች ከተፈኑ ተማሪዎች ዉጤት ጋር ያለውን ልዩነት ወይም ተቀራራቢነት በማየት እና በሚያገኘው ግኝት መሰረት የተማሪዎች ወደ የመንግስት ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በሚያስገባው መቁረጫ ዉጤት ላይ የሚኖረውን ተጽእኖ ዳግም እንዲያይ ሲልም በመግለጫው ጠይቋል።