በዚህ ዓመት የመንግስት ዩኒቨርስቲዎችን ከሚቀላቀሉት ያልተናነሱ ተማሪዎች በግል ይማራሉ ተባለ
152 ሺ 14 ተማሪዎች በመንግስት ዩኒቨርስቲዎች በመደበኛው ፕሮግራም ምደባ እንደሚያገኙ ሚኒስቴሩ አስታውቋል
135 ሺ 209 ተማሪዎች በተለያዩ አማራጮች ከፍተኛ ትምህርት መማር ይችላሉ ተብሏል
በዚህ ዓመት የመንግስት ዩኒቨርስቲዎችን ከሚቀላቀሉት ያልተናነሱ ተማሪዎች በግል ተቋማት ይማራሉ ተባለ፡፡
በዚህ አመት የ2013 ዓ.ም የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተናን ከወሰዱ ተማሪዎች ውስጥ 152 ሺ 14 ተማሪዎች በመንግስት ዩኒቨርስቲዎች በመደበኛው ፕሮግራም ምደባ እንደሚያገኙ ትምህርት ሚኒስቴር አስታውቋል።
ይህም በአማካይ በአጠቃላይ በሁለቱም ዙር ፈተናውን ወስደው 50 በመቶ እና ከዚያ በላይ ካመጡት ውስጥ 53 % ያህል ነው እንደ ሚኒስቴሩ ገለጻ።
በመንግስት ተቋማት ምደባ ከሚያገኙት ተማሪዎች ውስጥ 63 ሺ 833ቱ ሴቶች ናቸው ያለው ሚኒስቴሩ የዩኒቨርስቲ መግቢያ አነስተኛ ነጥብ እና ከዚያ በላይ ውጤት ያላቸው ሌሎች 135 ሺ 209 ተማሪዎች በተለያዩ አማራጮች ከፍተኛ ትምህርት መማር እንደሚችሉ አስታውቋል።
ይህም በዚህ አመት የመንግስት ዩኒቨርስቲዎችን ከሚቀላቀሉት ያልተናነሱ ተማሪዎች የግል የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትን ጨምሮ በሌሎች አማራጮች እንደሚማሩ የሚያሳይ ነው፡፡
የመልቀቂያ ፈተናውን በሁለቱም ዙር የወሰዱት 598 ሺ 679 ተማሪዎች ናቸው፡፡ ከነዚህም ውስጥ 50 በመቶና ከዚያ በላይ ያመጡት 287 ሺ 223 ናቸው ።
ሚኒስቴሩ በሁለት ዙር የተሰጠውን የ2013 ዓ.ም የዩኒቨርስቲ መግቢያ ፈተና ውጤት መቁረጫ ነጥብ ትናንት ሰኞ ይፋ ማድረጉ ይታወሳል።
ሆኖም መቁረጫ ነጥቡ በጦርነት ውስጥ የነበሩ አካባቢ ተፈታኞችን ታሳቢ ያደረገ አይደለም በሚል ቅሬታዎች እየቀረቡ ነው፡፡
በርካቶች በሁኔታው ሰለባ መሆናቸውንም ለአል ዐይን አማርኛ በሚልኳቸው መልዕክቶች አስታውቀዋል፡፡