አቶ እስክንድር በማረሚያ ቤት ድብደባ እንደደረሰባቸው ጠበቃቸው አረጋገጡ
አቶ እስክንድር ላይ ድብደባ ያደረሱት ታሳሪ ግለሰቦች መሆናቸውንም ጠበቃው አስታውቀዋል
በእነ እስክንድር ነጋ የክስ መዝገብ የተጀመረው ምስክርነት ድብደባው ምክንያት መቋረጡ ተገልጿል
በእስር ላይ የሚገኙት የባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ ፕሬዝዳንት እና የሰብዓዊ መብት አራማጅ እስክንድር ነጋ በማረሚያ ቤት ድብደባ እንደደረሰባቸው ተገለጸ።
በእነ እስክንድር ነጋ የክስ መዝገብ የተከሰሱ ተከሳሾች ምስክርነት የተጀመረ ቢሆንም አቶ እስክንድር በደረሰባቸው ድብደባ ምስክርነቱ መቋረጡ ተገልጿል።
- ፍርድ ቤቱ በእነ እስክንድር ነጋ ላይ የሚቀርቡ ምስክሮች ስም ዝርዝር እንዲገለፅ ወሰነ
- የተከሰሱበት ወንጀል የ14 ሰው ህይወት የጠፋበት ነው ያለው ፍርድ ቤቱ እነ እስክንድርን ዋስትና ከለከለ
የእነ አቶ እስክንድር ጠበቃ የሆኑት አቶ ሄኖክ አክሉሉ ከአል ዐይን አማርኛ ጋር ባደረጉት ቆይታ የባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ ፕሬዝዳንት እና የሰብዓዊ መብት አራማጅ አቶ እስክንድር መደብደባቸውን አረጋግጠዋል።
አቶ እስክንድር ላይ ድብደባ ያደረሱት ታሳሪ ግለሰቦች መሆናቸውን የባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ የድርጅት ጉዳይ ኃላፊ ስንታየሁ ቸኮል እንዳረጋገጡላቸው አቶ ሄኖክ ለአል ዐይን አማርኛ ገልጸዋል።
እነዚህ ግለሰቦች ለእነ አቶ እስክንድር ነጋ ደህንነታቸው አስጊ በመሆናቸው ወደ ቃሊቲ እንዲዛወሩ ተደርጎ እንደነበርም አቶ ስንታየሁ ቸኮል እንደገለጹላቸው ነው ጠበቃው አቶ ሄኖክ የተናገሩት።
አሁን ድብደባውን ፈጽመዋል የተባሉት ግለሰቦች እነ አቶ እስክንድር ወዳሉበት ቂሊንጦ በምን ምክንያት እንደመጡ አጠያያቂ መሆኑን ጠበቃው አቶ ሄኖክ ተናግረዋል።
የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 1ኛ የጸረ ሽብር እና ሕገ መንግሥታዊ ጉዳዮች ወንጀል ችሎት ጥቅምት 9 ቀን 2014 ዓ.ም በነበረው ውሎ ዐቃቤ ሕግ በእነ እስክንድር ነጋ ላይ የሚያቀርባቸው ምስክሮች ስም ዝርዝር በመገናኛ ብዙሃን እንዲገለፅ መወሰኑ ይታወሳል።
በዚህም መሰረት ምስክሮቹ ከጥቅምት 10 ቀን 2014 ዓ.ም ጀምሮ በግልፅ ችሎት እንዲመሰክሩ ተወስኖ የነበረ ሲሆን፤ አቶ እስክንድር በማረሚያ ቤት በደረሰባቸው ድብደባ ምክንያት ዛሬ ጥቅምት 11 ቀን 2014 ዓም ምስክር ሳይሰማ ቀርቷል ተብሏል።
አቶ እስክንድር ድብደባ እንደደረሰባቸውና ጉልበታቸው መቁሰሉን የቂሊንጦ ወህኒ ቤት የፈረቃ ኃላፊ ለፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ተናግረዋል ተብሏል።