የተከሰሱበት ወንጀል የ14 ሰው ህይወት የጠፋበት ነው ያለው ፍርድ ቤቱ እነ እስክንድርን ዋስትና ከለከለ
አቃቤ ህግ እነ እስክንድር ነጋ የተከሰሱበትን የወንጀል ክስ አሻሽሎ አቅርቧል
ፍርድ ቤቱ በ5ኛ ተራ ቁጥር ለተከሰሰው ጌትነት በቀለ ዋስትናን ፈቅዷል
የተከሰሱበት ወንጀል የ14 ሰው ህይወት የጠፋበት ነው ያለው ፍርድ ቤቱ እነ እስክንድርን ዋስትና ከለከለ
የእነ እስክንድርን የክስ ጉዳይ አሻሽሎ እንዲያቀርብ በፍርድ ቤት ታዞ የነበረው ዐቃቤ ህግ በትዕዛዙ መሰረት ክሱን አሻሽሎ አቀረበ።
የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ችሎት 1ኛ የህገ መንግስትና የጸረ ሽብር ጉዳዮች ወንጀል ችሎት ተከሳሾቹ ላይ የቀረበው የወንጀል ክስ የት ቦታ፣ በየትኛው ሰዓት እንደተፈጸመ እና የደረሰው የህይወትና የንብረት ጉዳት በዝርዝር ተሻሽሎ እንዲቀርብ በባለፈው ቀጠሮ አዝዞ ነበር፡፡
ዐቃቤ ህግም በታዘዘው መሰረት በቦሌ ክፍለ ከተማ ደረሰውን የንብረት ውድመት እንዲሁም በኮልፌ፣ በንፋስ ስልክ እና በሌሎችም ክፍለ ከተሞች የደረሰውን የሰው ህይወት መጥፋትና የንብረት ውድመት ክስ አሻሽሎ አቅርቧል።
የተሻሻለው ክስ እስክንድር ነጋን ጨምሮ ለ5 ተከሳሾች የደረሰ ሲሆን የክሱ ጭብጥ ለችሎቱ በንባብ ቀርቧል።
የሰው ህይወት አልጠፋም በተባለበት ቂርቆስ ክፍለ ከተማ በተፈጠረው ሁከትና የእርስ በርስ ግጭት ተሳትፎ አለው ተብሎ በ5ኛ ተራ ቁጥር የተከሰሰው ጌትነት በቀለ የተከሰሰበት ወንጀል ዋስትና እንደማያስከለክለው ፍርድ ቤቱ ገልጿል።
በመሆኑም ተከሳሹ የ30 ሺህ ብር የገንዘብና የሰው ዋስ አስይዞ ጉዳዩን በውጭ ሆኖ እንዲከታተል ነገር ግን ከሀገር እንዳይወጣ ገደብ ተጥሎበታል እንደ ፋና ብሮድካስቲንግ ዘገባ።
ሌሎች ተከሳሾች የተከሰሱበት ወንጀል ግን የ14 ሰዎች ህይወት የጠፋበት ነው ያለው ችሎቱ ክሱ ዋስትና እንደሚያስከለክል በመግለጽ የዋስትና ጥያቄያቸውን ውድቅ አድርጓል።
ስለሆነም እስክንድርን ጨምሮ ቀሪዎቹ ተከሳሾች ባሉበት ማረሚያ ቤት ሆነው ጉዳያቸውን እንዲከታተሉ ወስኗል።
የተከሳሽ ጠበቆች እስከ መስከረም 29 ቀን 2013 ዓ/ም ድረስ የክስ መቃወሚያቸውን በጽህፈት ቤቱ ማስገባት ይችላሉ ያለም ሲሆን አቃቤ ህግ መቃወሚያቸውን በዕለቱ ተቀብሎ ለጥቅምት 12 እንዲያቀርብ ሲል ተለዋጭ ቀነ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡