ማዕቀቡ የፕሬዝዳንት ፑቲን ደጋፊ ናቸው በሚል የተጣለ ነው
ብሪታንያ በሩሲያ ኦርቶዶክስ ፓትርያርክ ክሪል ላይ ማዕቀብ ጣለች፡፡
ማዕቀቡ ፓትርያርክ ክሪል የሩሲያ ጦር በፕሬዝዳንት ፑቲን ትዕዛዝ በዩክሬን በማካሄድ ላይ ያለውን "ዘመቻ" ደግፈዋል በሚል የተጣለ ነው።
የአውሮፓ ህብረት ሳይቀር በ75 ዓመቱ ፓትርያርክ ላይ ማዕቀብ መጣሉ ይታወሳል፡፡
የብሪታንያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሊዝ ትረስ ማዕቀቡን ፓትርያርክ ክሪልን ጨምሮ የፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ደጋፊና ተባባሪ ናቸው ባሏቸው ሩሲያውያን የመንግስትና ወታደራዊ ባለስልጣናት ላይ መጣላቸውን አስታውቀዋል፡፡
እንደ ሊዝ ትረስ ገለጻ ማዕቀቡ በሩሲያ የህጻናት መብት ኮሚሽነር ላይም ተጥሏል፡፡ ኮሚሽነር ማሪያ ልቮቫ ቤሎቫ ዩክሬናውያን ህጻናት በአስገዳጅ ሁኔታ እንዲዘዋወሩ እና በማደጎ እንዲሰጡ ፈቅደዋል በሚል ነው ማዕቀቡ የተጣለባቸው፡፡
ከብሪታኒያ እስከ አዘርባጃን፡ ፑቲን "ተደርገውብኝ ነበር" ካሏቸው አምስት የግድያ ሙከራዎች እንዴት ተረፉ?
2 ሺ ዩክሬናውያን ህጻናት ከዶኔስክ እና ሉሃንስክ አካባቢዎች በግድ ወደ ሩሲያ እንዲወሰዱ መደረጉንም ያትታል ማዕቀቡን አስመልክቶ የወጣው መግለጫ፡፡
ማዕቀቡ ከፓትርያርክ ክሪል እና ከኮሚሽነር ማሪያ በተጨማሪ የሞስኮ የምክር ቤት (ዱማ) አባላትን፣ የትራንስፖርት ኃላፊዎችንና አራት ኮሎኔሎችን ያካተተ ነው፡፡
ማዕቀቡን አስመልክተው አስተያየት የሰጡት ሊዝ ትረስ ዩክሬን ስኬታማ እስክትሆን ድረስ በፑቲንና በተባባሪዎቹ ላይ ጫና ማሳደራችን ይቀጥላል ብለዋል፡፡
ብሪታኒያ ከአሁን ቀደም የፑቲን የቅርብ አጋር ናቸው ባለቻቸው የሩሲያ ቱጃሮች ላይ ዐይነተ ብዙ ማዕቀቦችን መጣሏ ይታወሳል፡፡
ሩሲያ ማዕቀቡን በተመለከተ ይህ ዜና እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ የሰጠችው የአጸፋ ምላሽ የለም፡፡