ዩክሬን ከሩሲያ ኦርቶዶክስ ቤተ-ክርስትያን ጋር ግንኙነት አላቸው ባለቻቸው 22 ሰዎች ላይ ማዕቀብ ጣለች
ኬቭ ማዕቀቡን የጣለችው በኃይማኖት ሽፋን "የዘር ማጥፋት ዘመቻን" ደግፈዋል በሚል ነው
ባለፈው ዓመት ዩክሬን የሩሲያ ኦርቶዶክስ ቤተ-ክርስትያን ፓትርያርክ ኪሪል ላይ ማዕቀብ ጥላለች
ዩክሬን ከሩሲያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ጋር ግንኙነት አላቸው ባለቻቸው 22 ሩሲያውያን ላይ ማዕቀብ ጥላለች።
ፕሬዝዳንት ቮሎዲሚር ዘለንስኪ ሩሲያዊያኑ በኃይማኖት ሽፋን "የዘር ማጥፋት ዘመቻን" ደግፈዋል ብለዋል።
"በመንፈሳዊነት ሽፋን ሽብርተኝነትን እና የዘር ማጥፋት ፖሊሲን በሚደግፉ 22 የሩስያ ዜጎች ላይ ማዕቀብ ተጥሏል" ሲሉ ዘለንስኪ ተናግረዋል።
የዩክሬን ብሄራዊ ደህንነትና መከላከያ ምክር ቤት ባወጣው አዋጅ መሠረት፤ ማዕቀቡ በጄኔቫ የዓለም አብያተ ክርስቲያናት ምክር ቤት እና ሌሎች ዓለም አቀፍ ድርጅቶች የሩሲያ ኦርቶዶክስ ቤተ-ክርስቲያንን ተወካይ የሆኑትን ሚካሂል ጉንዳዬቭን ያጠቃልላል።
ጉንዳዬቭ የሩስያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን መሪ ፓትርያርክ ኪሪል የእህት ልጅ እንደሆኑ የሩስያ መንግስት መገናኛ ብዙሃንን ዋቢ በማድረግ ሮይተርስ ዘግቧል።
ባለፈው ዓመት ዩክሬን በፓትርያርክ ኪሪል ላይም ማዕቀብ ጥላለች።
አዲሱ ማዕቀብ ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን "ልዩ ተልዕኮ" ያሉትን ጦርነት "በመደገፍ" ዩክሬን በሩሲያ ኦርቶዶክስ ቤተ-ክርስቲያን ላይ የወሰደችው ተከታታይ እርምጃ ትልቁ አካል ነው ተብሏል።
ፕሬዝዳንት ዘለንስኪ የቅጣት እርምጃው የሀገሪቱን “መንፈሳዊ ነፃነት” ያጠናክራል ብለዋል።
አብዛኛዎቹ ዩክሬናውያን ኦርቶዶክስ ክርስቲያኖች ሲሆኑ በታሪክ ከሞስኮ ጋር ግንኙነት ባለው የቤተ-ክርስቲያኑ ቅርንጫፍና ከሶቪየት ህብረት መፍረስ በኋላ በተመሠረተው ገለልተኛ ቤተ-ክርስቲያን መሀል ፉክክር አለ ተብሏል።