ይህ የኢትዮጵያ ፓርክ በዱር እንስሳት ስብጥር ከአፍሪካ ሁለተኛ እንደሆነ መረጃዎች ያመለክታሉ
ከአዲስ አበባ በ 776 ኪ.ሜ ርቀት ላይ በምዕራብ ኢትዮጵያ የሚገኘው የጋምቤላ ብሔራዊ ፓርክ የዱር እንስሳትን ለመጠበቅ በሚል በ 1960 ዓ.ም መቋቋሙን ሰነዶች ይገልጻሉ፡፡
ይህ ፓርክ 4 ሺ 575 ስኩዌር ኪሎ ሜትር የሚሸፍን ፣ 69 አይነት አጥቢዎች ፣ 327 የተለያዩ የወፍ ዝርያዎች እና 7 አይነት ተሳቢ እንስሳት እንዲሁም 493 የእፅዋት ዝርያዎች በውስጡ ይገኛሉ፡፡ ዋልያ አይቤክስ ፣ የዱር አጋዘን ፣ የዱር አንጋላ ፣ ጎሽ ፣ ቀይ ቀበሮ እና ሌሎችም በፓርኩ ከሚገኙ እንስሳት መካከል ተጠቃሽ ናቸው፡፡ ይህ ፓርክ በዱር እንስሳት ስብጥር ከአፍሪካ ሁለተኛ እንደሆነም መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡
ፓርኩ ምንም እንኳን በውስጡ ብዙ አይነት የዱር እንስሳት ቢኖሩትም እየተደረገ ያለው ከመጠን ያለፈ ሕገ-ወጥ አደን የፓርኩን ህልውና እየተፈታተነ ነው፡፡ የኢትዮጵያ የዱር እንስሳት ልማት እና ጥበቃ ባለስልጣን ባለፈው ዓመት ብቻ በፓርኩ ወስጥ የሚገኙ አምስት ዝሆኖች መገደላቸውን አስታውቋል፡፡ ባለሥልጣኑ "በጋምቤላ ብሔራዊ ፓርክ የብዝሃ ህይወት ሀብት ላይ እየደረሰ ያለውን ጉዳት ለመከላከል የባለድርሻ አካላት የተቀናጀ ትብብር ያስፈልጋል" ብሏል።
የፓርኩ ጽህፈት ቤት ከፍተኛ ባለሙያ አቶ ሄኖከ ታምሩ ፣ በፓርኩ በሚገኙ የእንስሳት ሀብት ላይ ከፍተኛ ህገ ወጥ አደን እየተካሄደ መሆኑን ገልጸው በተለይም የነጭ ጆሮ ቆርኪ እና ዝሆኖች ላይ ከፍተኛ አደን እየተካሄደ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡
ሄኖክ ታምሩ-ቴሌስኮፕ የያዘው
አቶ ሄኖክ "ችግሩን ለመከላከል ጥረት እየተደገ ቢሆንም የተፈለገውን ያህል ለውጥ ማምጣት አልተቻለም" ብለዋል።
በፓርኩ ዙሪያ በቅርቡ በተደረገ ውይይት ላይ ፣ የቀድሞ የፓርኩ ጽህፈት ቤት ኃላፊ የአሁኑ የጋምቤላ ዩኒቨርሲቲ ምክትል ፕሬዚዳንት ጋልዋክ ኮርት (ዶ/ር) ፣ ቀደም ሲል በፓርኩ ከ550 በላይ ዝሆኖችና ከ 1 ሚሊዮን በላይ የነጭ ጆሮ ቆርኪዎች እንደነበሩ ገልጸዋል፡፡ አሁን ግን የዝሆኖችም ሆነ የነጭ ጆሮ ቆርኪና የሌሎች እንስሳት ቁጥር እየቀነሰ እንደሚገኝ አመልክተዋል፡፡
የክልሉ ባህልና ቱሪዝም ምክትል ቢሮ ኃላፊ ሎው ኡቡፕ (ዶ/ር) ደግሞ ፣ የፓርኩን ወሰን ግምት ውስጥ ያላስገባ የግብርና ኢንቨስትመንት፣ ህገ ወጥ ሰፈራ ፣ አደንና ሌሎች ድንበር ዘለል የአርብቶ አደሮች ጥቃት መኖሩን በውይይቱ ወቅት የገለጹ ሲሆን ይህን ለመከላከል እንደሚሰራ ጠቅሰዋል፡፡
ኢትዮጵያና ደቡብ ሱዳንን የሚያዋስነው ባሮ አኮቦ ወንዝን በማቋረጥ 1 ነጥብ 5 ሚሊዮን የሚገመት ነጭ ጆሮ ቆርኬዎች በክረምት ወቅት ከጋምቤላ ብሄራዊ ፓርክ ወደ ደቡብ ሱዳን ቦማ ብሔራዊ ፓርክ የሚያደርጉት የስደት ጉዞ አስደማሚ ትዕይንት ሲሆን ይህም ከዓለም ሁለተኛው መሆኑን የፓርኩ ጽህፈት ቤት ከፍተኛ ባለሙያ አቶ ሄኖከ ታምሩ ለአል ዐይን ተናግረዋል፡፡ በዚህ ወቅትም የእንስሳቱ የስደት ትዕይንት በሄሊኮፍተር የሚጎበኝ ፣ ደማቅና ማራኪ እንደሆነም ይገለጻል፡፡
ታንዛኒያና እና ኬንያን የሚያዋስነው ማራ ወንዝን በማቋረጥ ከታንዛኒያው ሰረንጌቲ ብሔራዊ ፓርክ ወደ ኬንያው ማሳማራ ብሔራዊ ፓርክ እርጥብ ሳር ፍለጋ በየአመቱ 2 ነጥብ 5 ሚሊዮን ዋይልድ ቢስቶች የሚያደርጉት የእንስሳት የስደት ትዕይንት በዓለም ላይ አንደኛ ሆኖ የተመዘገበ ሲሆን የኢትጵያው ደግሞ ሁለተኛ ነው፡፡
በክረምት ወቅት የጋምቤላ ብሔራዊ ፓርክ በውሃ ስለሚጥለቀለቅ እንስሳቱ ወደ ደቡብ ሱዳን ይሻገሩና ክረምቱ ሲያልፍ ተመልሰው ወደ ቀደመ ስፍራቸው ተመልሰው እንደሚመጡ አቶ ሄኖክ ገልጸዋል፡፡ በፓርኩ የመሰረተ ልማት ችግር በመኖሩ ትዕይንቱን ለመመልከት ቱሪስቶች ወደስፍራው መምጣት አለመቻላቸውን የገለጹት አቶ ሄኖክ የሀገር ውስጥና የውጭ ባለሀብቶች አካባቢውን ለማልማት ቢያስቡም በመሰረተ ልማት ችግሮች ምክንያት ፓርኩን ሳይመርጡት ቀርተዋል ብለዋል፡፡ በሄሊኮፕተር ብቻ የሚጎበኘው ይህ ፓርክ በቀጣይ በሌሎች የትራንስፖርት አማራጮችም መጎብኘት ይችል ዘንድ የመንግስትን እጅና ውሳኔ እየጠበቀ ነው፡፡