በኢትዮጵያ ብሔረሰቦች ላይ የተደረጉ ጥናታዊ ሰነዶች ለወመዘክር ተመለሱ
ለባለፉት ከ30 የሚልቁ አመታት በቦርዱ ተጠብቀው የቆዩት ጥናታዊ ሰነዶቹ በአምስት የተለያዩ ዘርፎች በአምስት ምሁራን ዋና መሪነት የተካሄዱ ናቸው
ጥናታዊ ሰነዶቹ የተመለሱት ሰነዶቹን ወርሶ በቆየው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ነው
መጋቢት 1975 ዓ.ም በቀድሞው መንግሥት አስተዳደር በተቋቋመው የብሔረሰቦች ጥናት ተቋም የተደረጉ ጥናታዊ ሰነዶች ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ቤተ-መዛግብትና ቤተ-መጻሕፍት ኤጀንሲ (ወመዘክር) ተመለሱ፡፡
ጥናታዊ ሰነዶቹ የተመለሱት ሰነዶቹን ወርሶ በቆየው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ነው፡፡
ቦርዱ መዛግብቱን ለኤጀንሲው ለማስረከብ ሲወስን በጉዳዩ ላይ የበለጠ መረዳትና ምርምር ማድረግ የሚሹ አካላት በቀላሉ ሊያገኛቸው በሚችሉበት ቦታ ማስቀመጡ ያለውን ጠቃሜታ በመረዳት እንደሆነ አስታውቋል።
ሦሥት ሺህ የሚጠጉ ወረቀቶች፣ ጥራዞች፣ ፎቶግራፎች እና የኦዲዮ ሰነዶች ናቸው ለኤጀንሲው ተመልሰው የተሰጡት፡፡
ጥናቶቹ በተለያዩ አምስት ዘርፎች ማለትም በታሪክ፣ በባሕል እና ቋንቋ ጥናት፣ በማኅበራዊ፣ በአስተዳደር፣ በምጣኔ ሃብት እና ሕገ-መንግሥትን በተመለከቱ ዘርፎች ላይ የተካሄዱ ናቸው፡፡
በዋናነት በአምስት ምሁራን መሪነት የተሰሩ ሲሆን በሥራቸው ከአምስት በላይ በከፍተኛ ደረጃ ከዩኒቨርስቲ የተመረቁ ወጣት ተመራማሪዎች ተሳትፈውበታል።
መዛግብቱን የመመለሱ የርክክብ ሥነ-ሥርዓትም ትናንት ሰኞ ታኅሣሥ 12 ቀን 2013 ዓ.ም የቦርዱ ሰብሳቢ ብርቱካን ሚደቅሳ እና የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር አቶ ይኩኖአምላክ መዝገቡ እንዲሁም በወቅቱ ጥናቱን ያካሄዱት ምሁራን በተገኙበት ተካሂዷል።
በሥነ-ሥርዓቱ አጥኚ ምሁራኑ ሀሳባቸውን ያካፈሉ ሲሆን መዛግብቱን ለእንግዶች ክፍት በማድረግ ተጠናቋል።