ብዙ ሚዲያዎችና ሌሎች አካላት መንግስት ለሚሰራው የመልሶ ማቋቋም ስራ “በፍጹም እውቅና አይሰጡም” አምባሳደር ዲና
መንግስት በትግራይ ክልል ሰብዓዊ ድርጅቶችና ሚዲያዎች የተሟላ ተደራሽነት እንዳይኖራቸው አድርጓል በሚል ይተቻል
አምባሳደር ዲና ለታዳጊ ሀገራት “ትኩረት ከተሰጠም ለአሉታዊ ዜናዎች ነው” ሲሉ ገልጸዋል
በትግራይ ክልል ካለው ወቅታዊ ሁኔታ ጋር በተያያዘ በተለያዩ አካላት የሚነሱ ሀሳቦችን በተመለከተ አስተያየት የሰጡት አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ፣ ገና ውጊያው ሲጀመር በርካታ ሰብዓዊ ድጋፍ ሰጪ ድርጅቶችን ጨምሮ የተለያዩ አካላት “ይሔ ጦርነት ይራዘማል ፤ በአጭር ጊዜ ውስጥ አይቋጭም ፤ ሌሎችንም የቀጣናውን ሀገራት ያዳርሳል የሚል ሀሳብ ሲሰጡ ነበር” ብለዋል፡፡
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባዩ አምባሳደር ዲና በኢቲቪ የቀጥታ ስርጭት ላይ ቀርበው እንዳሉት ፣ እነዚሁ ሰብዓዊ ድርጅቶች እና ሌሎች አካላት በርካታ ውድመት እንደሚኖር እና ብዙ ህዝብ እንደሚፈናቀል ነበር የሚያነሱት፡፡ በውጭ ግንኙነት ቻናሎች አማካኝነት ለሚኒስቴር መስሪያ ቤቱም ተመሳሳይ ሀሳቦች በተደጋጋሚ ይቀርቡ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡
ይሁን እንጂ ስለ ጦርነቱ መራዘም እና ስለመዘዙ አስከፊነት የሚያነሱት ሰግተው ነው ወይስ ከመራዘሙ የሚጠቀሙት ነገር ስላለ ነው የሚለውን ባለሙያዎች ሊመራመሩ እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡
አምባሳደር ዲና የራሳቸውን ምክንያት ሲገልጹ ፣ በታዳጊ ሀገራት የሚኖሩ ችግሮች ፣ መፈናቀሎች እና በውስጥም በውጭም የስደት ካምፖች መኖራቸው መልካም ዕድል የሚፈጥሩላቸው በርካታ ተቋማት በውጪው ዓለም ፣ በተለይ በምዕራቡ ዓለም ስለመኖራቸው ያነሳሉ፡፡
ሲጀመር ፣ በሚዲያዎች እና በተለያዩ ድርጅቶች ፣ ለታዳጊ ሀገራት የሚሰጠው ትኩረት አናሳ መሆኑን የገለጹት አምባሳደር ዲና “ትኩረት ከተሰጠም ለአሉታዊ ዜናዎች ነው” ይላሉ፡፡ እነዚህም መፈናቀል ፣ መጣላት ፣ ጦርነት ፣ ርሀብ እና እልቂትን የመሳሰሉ መሆናቸውን አንስተዋል፡፡ የሚሸጠው ዜናም ይሔው እንደሆነ ነው አምባሳደር ዲና የገለጹት፡፡
ችግር ወደ ተከሰተበት ሄደው የማቋቋም ፣ የማደራጀት ፣ እርዳታ የማሰባሰብ ተልዕኮ አስበው የሚንቀሳቀሱ አካላት እንዳሉም አምባሳደር ዲና በንግግራቸው ጠቁመዋል፡፡ ይህን መሰል ዓላማቸው ባለመሳካቱ የከፋቸው ሰዎች “በኢትዮጵያ ውጊያው ማለቁን መቀበል አይፈልጉም” ሲሉም ገልጸዋል፡፡ “ምንም እንኳን የተደበቁ ኃይሎች እዚህም እዚያም የሚፈጥሩት ግጭት ቢኖርም ዋናው ጦርነት አልቋል” ያሉት ቃል አቀባዩ ይሁንና ብዙ ድርጅቶች እና ሚዲያዎች ”ጦርነት ማለቁን ካለመቀበል ባለፈ አሁንም ጦርነት እንዳለ አድርገው ነው የሚያቀርቡት” ብለዋል፡፡ በመሆኑም “በጦርነቱ መቀጠል ተጠቃሚ የሚሆኑ ኃይሎች አሉ ብለን ነው የምንወስደው” ሲሉ ሆን ተብሎ የሀሰት መረጃ የማሰራጨት ስራ እንደሚከናወን ጠቁመዋል፡፡
መንግስት በአሁኑ ወቅት ተፈናቃዮችን ለማቋቋም የሚያደርጋቸው ጥረቶች ስለመኖራቸውም ያነሱት አምባሳደር ዲና የጦርነቱን ማብቃት የማይቀበሉ አካላት ለመልሶ ማቋቋም ስራውም “በፍጹም እውቅና አይሰጡም” ነው ያሉት፡፡ “መንግስት የሚያደርሳቸው የሰብዓዊ እርዳታዎችንም አይቀበሉም ፤ በፍጹም አልደረሰም ነው የሚሉት፡፡ ሰው እያለቀ ነው ፤ ጦርነት ነው ፤ ውድመት ነው ፤ በክልሉ ርሀብ ነው ያለው” የሚል ሀሳብ ብቻ እንደሚያስተጋቡም ተናግረዋል፡፡
“በመንግስት በኩል እዛ አካባቢ ችግር የለም አልተባለም” የሚሉት አምባሳደር ዲና የሕግ የበላይነትን ለማስከበር ወታደራዊ እንቅስቃሴ የተካሔደበት አካባቢ እንደመሆኑ “መፈናቀል ፣ ሞት ፣ ዝርፊያ እና የመሳሰሉ ችግሮች አሉ” ብለዋል፡፡ ሕወሓት ከክልሉ ኃላፊነት ሲነሳ 13,000 ያህል እስረኞች መለቀቃቸውንም እንደ አንድ የቀውስ ምክንያት አስቀምጠዋል፡፡ “የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ሙሉ በሙሉ ያላስከበረው ቦታ አለ ፤ እዛ አካባቢ ክፍተቶች ቢፈጠሩ እና ህገወጥ ስራዎች ቢሰሩ የሚገርም አይደለም” ሲሉም አምባሳደር ዲና ገልጸዋል፡፡ አክለውም “አስገድዶ መድፈር ሊኖር ይችላል ግን መርምረን ተጠያቂውን አካል ለሕግ እናቀርባለን ነው መንግስት እያለ ያለው” ብለዋል፡፡
በኢትዮጵያ በመሬት ላይ ያሉ እውነታዎችን ከማዛባት ባለፈም “አዎንታዊ የሆነን ነገር ሁሉ የመዘገብ ፍላጎት እንደሌለ” ያነሱ ሲሆን በታዳጊ ሀገሮች ሁሉ ጦርነት ፣ መፈናቀል እና ተመሳሳይ ችግሮች የሚዘገቡትን ያህል ከጦርነት ወጥተው ጥሩ ደረጃ ላይ ስለሚገኙ ሀገራት የሚባል ነገር እንደሌለ አምባሳደር ዲና ይገልጻሉ፡፡ ይህ የሚሆነው “ከዚህ ተጠቃሚ ስላለ ነው” ሲሉም ምክንያታቸውን አስቀምጠዋል፡፡ “ሁሉንም የረድኤት ድርጅቶች አይደለም እየከሰስኩ ያለሁት፡፡ ነገር ግን ከቀውሶች የሚጠቀሙ አካላት ስላሉ ይህን የሚያራግቡላቸው ሚዲያዎችም አሉ” ብለዋል፡፡
በተለያዩ ሀገራት የሚገኙ የኢትዮጵያ ኤምባሲዎች እና ሚሲዮኖች በኢትዮጵያ ስላለው ሁኔታ ትክክለኛውን መረጃ ለሚመለከታቸው አካላት የመስጠት ተልዕኮ ወስደው በመስራት ላይ እንደሚገኙም አምባሳደር ዲና ገልጸዋል፡፡ ተመሳሳይ ተግባር የሚያከናውኑ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያንንም የማገዝ ስራ እንደሚሰሩ ነው ያብራሩት፡፡
በትግራይ ክልል የተፈጠረውን ቀውስ ተከትሎ ሰብዓዊ እርዳታ ለማድረስ ወደ ክልሉ በርካታ አካባቢዎች እንዳንገባ ተከልክለናል በማለት በርካታ የሰብዓዊ እርዳታ ድርጅቶች በኢትዮጵያ መንግስት ላይ ወቀሳ ያስሰማሉ፡፡ ክልሉ ለሚዲያ አካላትም ሙሉ በሙሉ ክፍት አልሆነም በሚል ትችቶች መነሳታቸውን ቀጥለዋል፡፡ የተባበሪት መንግስታትን ጨምሮ በርካታ ሀገራት እና ተቋማት ፣ ለሰብዓዊ ድርጅቶች ክልሉ ሙሉ በሙሉ ክፍት እንዲሆን በተደጋጋሚ ጥሪ ቢያቀርቡም መንግስት በሰብዓዊ ድርጅት አማካኝነት ሌላ ተልዕኮ የመፈጸም ፍላጎት እንዳለ ሲገልጽ ቆይቷል፡፡ ይሁንና መንግስትና ሰብዓዊ አጋሮች እ.ኤ.አ. ህዳር 29/ 2020 በተፈራረሙት የመግባቢያ ስምምነት መሰረት በቅንጅት እየሰሩ እንደሚገኙ የኢትዮጵያ መንግስት አስታውቋል፡፡