ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ ከቢሮ በፖሊስ መወሰዱን ወንድሙ ታሪኩ አስታወቀ
ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ ከቢሮ በፖሊስ መወሰዱን ወንድሙ ታሪኩ አስታወቀ
የፍትሕ መጽሔት ማኔጅንግ ዳይሬክተር ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ ዛሬ ከቀኑ ስምንት ሰዓት አካባቢ ቢሮው በመጡ ፖሊሶች መያዙን ወንድሙ ገለጸ፡፡
የተመስገን ደሳለኝ ወንድም ታሪኩ ደሳለኝ ፖሊሶች ፍትሕ መጽሔት ወደሚገኝበት አድዋ ድልድይ አካባቢ ሄደው ተመስገን ያለበትን ቦታመጠየቃቸውን ገልጿል፡፡ በሰዓቱ ጋዜጠኛ ተመስገን ቢሮ ውስጥ እንዳልነበር የገለጸው ታሪኩ ደሳለኝ የመጽሔቱ አዘጋጅ ለተመስገን ስልክ መደወሉን በፌስቡክ ገጹ ገልጿል፡፡
ከፖሊሶቹ ውስጥ አንዱ ተመስገንና አዘጋጁ ስልክ እያወሩ ሳለ ስልኩን ተቀበሎ እንደሚፈልጉት እና የት እንደሚገኝ መጠየቁን ገልጿል፡፡
ተመስገንም ይዘው የመጡት መጥሪያ ወይም ክስ ካለ ቢሮ አስቀምጠው እንዲሄዱ እንደነገራቸው ነው ታሪኩ የተናገረው፡፡ በስልክ ያናገረው ፖሊስ ግን የሚፈልጉት እርሱን እንደሆነና ያለበትን እንዲነግራቸው የጠየቃቸው ሲሆን እርሱም “ግድ የለም እኔን ከፈለጋችሁኝ ቢሮ እመጣለሁ” የሚል
ምላሽን ሰጥቶ ወደ ቢሮው ተመለሰ።ተመስገን ቢሮ እንደደረሰም ወስደውታል ብሏል፡፡
ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ አዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን መታሰሩን በር ላይ ካሉት ፖሊሶች ማረጋገጡንም የጋዜጠኛው ወንድም ታሪኩ ደሳለኝ ዘግይቶ ገልጿል፡፡
ባለፈው ቅዳሜ በወጣችሁ ፍትሕ መጽሔት ላይ “አባ ብላ ገመዳ ” በሚል ርዕስ በተጻፈው ጹሑፍ ዙሪያ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ጽ/ቤት ለብሮድካስት ባለስልጣን የቅሬታ ደብዳቤ ጽፎ ነበር፡፡ጋዜጠኛ ተመስገን ከዚህ በፊት በተደጋጋሚ ለእስር ተዳርጎ እንደነበር የሚታወስ ሲሆን ከዚህ በፊት ፍትሕ ጋዜጣ፣ፋክት መጽሄትና ሌሎችንም ሲያዘጋጅ እንደነበር ይታወሳል፡፡