በዱባይ ኤክስፖ 2020 ላይ ሉሲን ይዞ የቀረበው የኢትዮጵያ እልፍኝ በበርካቶች እየተጎበኘ ነው ተባለ
ለ6 ወራት በሚቆየው ዱባይ ኤክስፖ ላይ ኢትዮጵያን ጨምሮ 192 በላይ ሀገራት እየተሳተፉ ነው
ጤፍና የኢትዮጵያ ቡና አፈላል የበርካቶችን ቀልብ መሳቡን የዱባይ ንግድ ምክር ቤት የኢትዮጵያ ቢሮ ኃላፊ ተናግረዋል
ኢትዮጵያን ጨምሮ 192 በላይ ሀገራት እየተሳተፉበት የሚገኘው የዱባይ ኤክስፖ 2020 ከተከፈተ አንድ ወር ሞልቶታል።
የዱባይ ንግድ ምክር ቤት የኢትዮጵያ ቢሮ ኃላፊ ተዋበች ኃይሉ፤ በዱባይ ኤክስፖ 2020 ላይ የኢትዮጵያ ተሳትፎ ምን ይመስላል በሚለው ላይ ለአል ዐይን ኒውስ ማብራሪያ ሰጥተዋል።
ዱባይ ኤክስፖ 2020 በቀጠናው ግዙፍ ከሆኑ ሁነቶች አንዱ መሆኑን የተናገሩት ኃላፊዋ፤ በዱባይ ኤክስፖ 2020 ኢትዮጵያ ቆንጆ የሆነ እልፍኝ (ፕቪሊየን) እንዳላትም ተናግረዋል።
የኢትዮጵያን አልፍኝ መጎብኘታቸውን የሚናገሩት ኃላፊዋ፤ በርካታ ኢትዮጵያን የሚገሉጹ ባህላዊ፣ ታሪካዊ እና የተለያዩ የቴክኖሎጂ ፈጠራዎች መቅረባቸውን ተናግረዋል።
የኢትዮጵያን አልፍኝ (ፕቪሊየን) ከሌሎች ለየት የሚያደርገው በርካቶች ስለ ቴክኖሎጂ ፈጠራዎች ሲያወሩ፤ የኢትዮጵያ ግን ስለ ታሪከ እና ስለ ምድረ ቀደምትነት የሚያወራ መሆኑ ነውም ብለዋል።
ድንቅነሽ (ሉሲ) በኤክስፖ 2020 ዱባይ ላይ ኢትዮጵያን ለማስተዋወቅ መቅረቧ ይታወቃል፤ ይንህንን በተመለከተም ኃላፊዋ፤ ሉሲ መቅረቧ የኢትዮጵያ እልፍኝ ለየት እንዲል እና በበርካቶች እንዲጎበኝ ካደረገው ውስጥ አንዱ መሆኑን ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ምግብ የሆነው እንጀራ ከምን ይሰራል የሚለውን ለማሳየትም ጤፍ መቅረቡን ያነሱ ሲሆን፤ ጤፍ ምንድነው የሚለውን ጎብኚዎች በእጃቸው ሁላ ነክተውት እንዲያውቁ እየተደረገ መሆኑንም ገልፀዋል።
የኢትዮጵያ ባህላዊ የቡና አፈላም በኤክስፖው ላይ ቀርቧል ያሉት ኃላፊዋ፤ በርካቶች የቡና አፈላሉን እየጎበኙት መሆኑን እና በብዙዎች ዘንድ እንደተወደደም አስታውቀዋል።
ባሳለፍነው ጥቅምት ወር የተጀመው እና ለቀጣይ ስድስት ወራት ማለትም እስከ ፊታችን መጋቢት ወር በሚቆየው ኤክስፖው ላይ ከ192 በላይ ሀገራት መሳተፋቸውን ይታወቃል።
ዱባይ ኤክስፖ 2020 ከተከፈተ በኋላ በበበርካቶች የተጎበኘ ሲሆን፤ እስከ ኤክስፖው ማጠናቀቂያ ድረስም እስከ 25 ሚሊየን በሚደርሱ ሰዎች እንደሚጎበኝም ይጠበቃል።
በአረብ ሀገራት ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ እየተካሄደ እንደሆነ የተነገረለት የዱባይ ኤክስፖ 2020 ከ10 ዓመት በላይ የፈጀ ዝግጅት ሲደረግ ቆይቷል።