ኢ/ር አይሻ መሀመድ የመከላከያ ሚንስትር ሁነው በድጋሚ ተሸሙ
የመከላከያ ሚኒስትር የነበሩት ዶ/ር አብርሃም በላይ የመስኖና ቆላማ አካባቢ ሚኒስትር ሁነዋል
ጠ;ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ዛሬ የተለያዩ ሚኒስትሮች ሹመቶች ሰጥተዋል
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በዛሬው ዕለት የተለያዩ ሹመቶችን መስጠታቸውን የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት አስታውቋል።
በዚሁ መሰረት ዶ/ር አብረሃም በላይን ከመከላከያ ሚኒሰትርነት ያነሱ ሲሆን፤ በእሳቸው ምትክም ኢ/ር አይሻ መሃመድን የመከላከያ ሚኒስትር አድርገው በድጋሚ ሾመዋል።
ኢንጂነር አይሻ በ2009 በተደረገው የሚኒስትሮች ሹመት ኮንስትራክሽን ሚኒስትር በመሆን ለሁለት ዓመታት ያገለገሉ ሲሆን ከዚያም ወደ መከላከያ ሚኒስትር ተዛውረው በሚኒስትርነት አገልግለዋል።
በዚህም ኢንጂነር አይሻ መሃመድ የመጀመሪያዋ ሴት የመከላከያ ሚኒስትር ሆነው 2011 ላይ ተሸመው የነበረ ሲሆን፤ ከወራት ቆይታ በኋላ ቀድሞ ወደ ነበሩበት የኮንስትራክሽን ሚኒስቴር ተመልሰው ነበር።
በመቀጠልም በ2014 አዲስ ካቢኔ ሲዋቀር ኢንጂነር አይሻ አይሻ መሃመድ የመስኖ እና ቆላማ አካባቢ ሚኒስትር ሆነው የተሸሙ ሲሆን፤ ዛሬ አዲስ ሹመት እስከሚሰጣቸው ድረስም በዚያው መስሪያ ቤት ሲያገለግሉ ቆይተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ አዲስ በሰጡት ሹመትም ኢንጂነር አይሻ መሃመድ ከግንቦት 13 ቀን 2016 ዓ.ም ጀምሮ እንደገና የመከላከያ ሚኒስትር ሁነው እንዲያገለግሉ ተመድበዋል።
የመከላከያ ሚኒስትር ሁነው በማገልገል ላይ የነበሩት ዶ/ር አብርሃ በላይ ደግሞ የኢንጂነር አይሻን ይመሩት የነበረውን የመስኖና ቆላማ አካባቢ ሚኒስትርን እንዲመሩ ተሹመዋል።
በተጨማሪም በኢትዮጵያ ዳያስፖራ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ሁነው ሲያገለግሉበት የነበሩት ዶ/ር መሀመድ እንድሪስ ፤ በሚኒስትር ዴኤታ ማዕረግ በዲሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ከግንቦት 13 ቀን 2016 ዓ.ም ተሹመዋል።