ጠ/ሚ አብይ አህመድ ከቻይናው ፕሬዝዳንት ሺ ጂንፒንግ ጋር ተወያዩ
መሪዎቹ የኢትዮጵያ እና ቻይናን ስትራቴጂካዊ ትብብር ለማሳደግ ተስማምተዋል
3ኛው የአንድ ቀበቶ አንድ መንገድ ፎረም በቤጂንግ እየተካሄደ ነው
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ከቻይናው ፕሬዝዳንት ሺ ጂንፒንግ ጋር ተወያዩ።
በ3ኛው የአንድ ቀበቶ አንድ መንገድ ፎረም ለመሳተፍ በቤጂንግ የሚገኙት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ እና ሚኒስትሮችን ያካተተው ልኡካቸው ከፕሬዝዳንት ሺ ጂንፒንግ ጋር ምክክር አድርጓል።
በዚህም ሀገራቱ በሁሉም ዘርፎች ስትራቴጂካዊ ትብብራቸውን ለማጠናከር መስማማታቸውን ሽንዋ ዘግቧል።
ባለፉት አስርት አመታት ኢትዮጵያ እና ቻይና በአንድ ቀበቶ አንድ መንገድ (ቤልት ኤንድ ሮድ) ትብብራቸውን ማሳደጋቸውን ያነሱት ፕሬዝዳንት ሺ፥ ኢትዮጵያ ለቻይና - አፍሪካ ትብብር መጎልበት ትልቅ ድርሻ እንዳላትም አብራርተዋል።
ቻይና እና ኢትዮጵያ ሁሉንም ተጠቃሚ የሚያደርግ፣ የደቡብ - ደቡብ ወንድማማችነትን የሚያጠናክር እና እኩልነትና ፍትህን የሚያረጋግጥ ሁሉን አቀፍ ስትራቴጂካዊ ትብብር ሊፈጥሩ እንደሚገባም ነው ፕሬዝዳንቱ የገለጹት።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በትናንትናው እለትም ከቻይናው ጠቅላይ ሚኒስትር ሊ ኬ ያንግ ጋር ተወያይተዋል።
በውይይታቸው ወቅትም በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን የምጣኔ ሀብት ትብብር ግንኙነት ማጠናከር በሚያስችሉ ጉዳዮች ዙሪያ መምከራቸውን የጠቅላይ ሚኒስትር ፅህፈት ቤት መረጃ ያመላክታል።
ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ የመንግስታቸውን ባለብዙ ዘርፍ የእድገት አላማ ብሎም የተገኙ ድሎችን በተመለከተ ገለጻ አድርገዋል።
በተጨማሪም ከቻይና ጋር የንግድ ግንኙነቶችን ማስፋፋት አስፈላጊ መሆኑን አፅንዖት ሰጥተው መናገራቸው ተጠቅሷል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ሊ ኬ ያንግ በበኩላቸው ፥ ሁለቱ ሀገራት በማደግ እና በመጎምራት ላይ ያለ ኢኮኖሚ ባለቤቶች እንደመሆናቸው በጋራ የማደጊያ መንገዶችን ሊቀይሱ እንደሚችሉ አንስተዋል።
ኢትዮጵያ እና ቻይና በተለያዩ መስኮች 12 ያህል የትብብር ስምምነቶችና ሁለት የፍላጎት ሰነዶች ተፈራርመዋል።