በሱዳንና በሌሎች ሀገራት የሚገኙ ተጠርጣሪዎቹን ለመያዝ ከሀገራቱ ጋር እየተነጋገርን ነው-ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን
ኮሚሽኑ በቅርቡ የጦር መሳሪያ ምዝገባ እንደሚጀምርም ገልጿል
ኮሚሽኑ ተጠርጣሪ ወንጀለኞችን ከሚፈለጉበት ሀገር ለማምጣት ከኢንተርፖል ጋር እየሰራ መሆኑን ገልጿል
የፌደራል ፖሊስ ምክትል ኮሚሽነር ዘላለም መንግስቴ እንዳሉት ሱዳንን ጨምሮ በሌሎች ሀገራት የተደበቁ ተጠርጣሪ ወንጀለኞች ተገቢውን ቅጣት እንዲያገኙ እየሰሩ መሆኑን ተናግረዋል።
በቅርቡ ከጅቡቲ መንግስት ጋር በተደረገ ውይይት ተጠርጣሪ ወንጀለኞችን አሳልፈው ሰጥተውናል ያሉት ምክትል ኮሚሽነሩ በሱዳን ፤በኬንያ እና በሌሎች ሀገራት ያሉ ተፈላጊ ተጠርጣሪዎችን ለመረከብ ውይይቶች በመደረግ ላይ መሆናቸውንም ተናግረዋል።
እንደ ምክትል ኮሚሽነሩ ገለጻ በትግራይ ክልል ከተፈጠረው ችግር ጋር ተያይዞ የሚፈለጉ ተጠርጣሪዎች ወደ ጎረቤት ሀገራት በመሸሽ በስደተኛ ጣቢያዎች ያሉትንም ሆነ ከዚያ በፊት የተለያዩ ወንጀሎችን በመፈጸም በሌሎች ሀገራት የተደበቁትን ለመያዝ ከሚኖሩባቸው ሀገራት እና ከዓለም አቀፉ የፖሊስ ተቋም ወይም ኢንተርፖል ጋር በይፋ ውይይት እየተደረገ ነው።
ተጠርጣሪዎቹን በህግ ቁጥጥር ስር ሀገራት እየተባበሩን እና ፈቃደኝነታቸውን እያሳዩን ነው ያሉን ምክትል ኮሚሽነር ዘላለም ሀገራቱ የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል ያስቀመጧቸው እርምጃዎች ስራቸውን እንዳስተጓጎለባቸው ነግረውናል።
ኮሮና ቫይረስ ባይከሰት ኖሮ እስካሁን በብዙ አገራት ያሉ ተጠርጣሪ ወንጀለኞችን ይረከቡ እንደነበር ገልጸዋል።
ህገወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውርን ለመቆጣጠር አዘዋዋሪዎችን ለመያዝ ጥብቅ ክትትል እየተደረገ እና እየተያዙ መሆኑንም ተናግረዋል።
ህገወጥ የጦር መሳሪያ አዘዋዋሪዎች በሁለት መንገድ ወደ ኢትዮጵያ የጦር መሳሪያ ያስገባሉ ያሉን ምክትል ኮሚሽነር ዘላለም አንደኛው እንደ አዋጭ የንግድ ዘርፍ በማየት ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ሀገርን ለማፍረስ በማሰብ ነው ብለዋል።
“ኮሚሽኑ ዝውውሩን ለማምከን ተጠርጣሪዎችን እየተከታተሉ ተገቢውን ቅጣት እንዲያገኙ እየተደረገ ነው። የጦር መሳሪያዎቹ ከሚመጡባቸው እንደ ቱርክ እና ሌሎች ሀገራት ጋር በመምከር ላይ ነን” ሲሉን ምክትል ኮሚሽነሩ ተናግረዋል።
ከዚህ ወንጀል ጋር በተያያዘ ኢትዮጵያ የምትፈልጋቸው ተጠርጣሪዎች በሱዳን፤ኬንያ ቱርክ እና ሌሎች ሀገራት እንዳሉ ስለሚታወቅ ተጠርጣሪዎቹን ለመያዝ ከሀገራቱ ጋር በመነጋገር ላይ መሆናቸውንም ገልጸዋል።
ከዚያ በተጨማሪም ባለፈው ዓመት በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በጸደቀው የጦር መሳሪያ አስተዳድር አዋጅ መሰረት የጦር መሳሪያ ምዝገባ እንደሚካሄድ ገልጸዋል።
ምዝገባውን ለመፈጸም የጦር መሳሪያ ዝውውር አዋጅ ደንብ እና መመሪያ እየተዘጋጀ መሆኑን የተናገሩት ምክትል ኮሚሽነሩ በቅርቡ ምዝገባው ይጀመራል ብለዋል።