የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን የዘረመል (ዲኤንኤ) ምርመራ ሊጀምር መሆኑን አስታወቀ
ኢትዮጵያ አስካሁን ድረስ የዘረመል ምርመራ የምታደርገው ወደ ደቡብ አፍሪካ እየላከች ነው
ምርመራውን በሀገር ውስጥ ለማከናወን በዓለም አቀፍ ጨረታ አሸናፊው ተለይቶ ስራው መጀመሩ ተገልጿል
የፌዴራል ፖሊስ ምክትል ኮሚሽነር ዘላለም መንግስቴ ለአል ዐይን አማርኛ እንዳሉት ኢትዮጵያ ከዘረመል ጋር የተያያዙ ምርመራዎችን ለመስራት በውጭ ምንዛሬ ወደ ደቡብ አፍሪካ እየላከች ነበር ስታከናውን የነበረው።
በተለይም ከሁለት ዓመት በፊት የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ናይሮቢ በማቅናት ላይ እያለ ቢሾፍቱ አካባቢ ተከስክሶ የሁሉም ተሳፋሪዎች ህይወት አልፎ የሰዎቹን ማንነት ለመለየት የግድ የዘረመል ምርመራ ማድረግ አስፈልጎ ነበር።
ይሁንና ይሄንን ማድረግ የሚያስችል የምርመራ ማዕከል ባለመኖሩ የግድ ወደ ውጭ ሀገራት መላክ ግዴታ ሆኖ እንደነበር ኮሚሽነር ዘላለም ተናግረዋል።
ይህ ለአብነት ይነሳ እንጂ ፣ “በሌሎችም ጉዳዮች ለፖሊስ የወንጀል ምርመራ ስራ የግድ የዘረመል ውጤት ሲያስፈልግ ወደ ውጭ ሀገራት እየላክን ነው ፤ ይህ ግን መቆም አለበት” ብለዋል ምክትል ኮሚሽነሩ።
“የፖሊስ አገልግሎት በኢትዮጵያ የረጅም ጊዜ ታሪክ ቢኖረውም ፣ ዘመኑን የሚመጥን ዘመናዊ የምርመራ ቴክኖሎጂ ግን የለም” ያሉት ምክትል ኮሚሽነር ዘላለም ፣ ተቋማቸው አሁን ላይ የተለያዩ የለውጥ ስራዎችን በማከሄድ ላይ መሆኑን ገልጸዋል።
ተቋሙ ለወንጀል ምርመራዎች ከሰው ማስረጃ ባለፈ የቴክኒክ እና የታክቲክ መረጃዎችን ማግኘት የሚያስችሉ ቴክኖሎጂዎችን በማሟላት ላይ መሆኑንም ነግረውናል።
ከነዚህ ስራዎች መካከልም “የዘረመል ምርመራ ፣ የፎረንሲክ እና ሌሎች ተያያዥ የቴክኖሎጂ መሳሪያዎችን እያሟላን ነው” ብለዋል።
የዘረመል ምርመራ አገልግሎትን በሀገር ውስጥ ለማከናወንም ዓለም አቀፍ ጨረታ ወጥቶ አሸናፊው ተለይቶ ስራው መጀመሩን ኮሚሽነር ዘላለም ገልጸዋል።
የዘረመል ምርመራው በአዲስ አበባ ባለው “ፖሊስ ሆስፒታል ውስጥ በመደራጀት ላይ ነው” ያሉን ምክትል ኮሚሽነሩ ፣ ማዕከሉ ከፖሊስ ምርመራ ባለፈ አገልግሎት ፈላጊ ግለሰቦችንም ያገለግላል ብለዋል።
በአዲስ አበባ ብቻ ተወስነው የነበሩት የአስከሬን እና የፎረንሲክ ምርመራ ስራዎች ወደ ክልል ከተሞች መውረዳቸውንም ገልጸዋል።
በቀጣይም ጊዜው የሚጠይቀውን የምርመራ ቴክኖሎጂ ማሟላታችንን እንቀጥላለንም ብለዋል።
የግድያ እና መሰል ወንጀሎችን ለማወቅ የአስከሬን ምርመራዎች የሚካሄዱት በሚኒሊክ እና ቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታሎች ሲሆን አገልግሎቱን በፖሊስ ሆስፒታል ለማስጀመር እንቅስቃሴ መጀመሩንም ምክትል ኮሚሽነር ዘላለም ተናግረዋል።
ፌዴራል ፖሊስ ቀጣዩን ሀገር አቀፍ ምርጫ ፍጹም ሰላማዊ በሆነ ሁኔታ ለማጠናቀቅ ዝግጁ መሆኑን ማሳወቁ ይታወሳል።
ከምርጫው ውጤት ይፋ መሆን ጋር ተያይዞ የጸጥታ ችግር ይከሰታል የሚል ዕምነት እንደሌለው ኮሚሽኑ የገለጸ ሲሆን ፣ ይሁንና ከምርጫው ውጤት ጋር ተያይዞ በኃይል ለመንቀሳቀስ የሚሞክር ግለሰብም ሆነ ተቋም ካለ ይህንን መቀልበስ የሚችል የሰው ኃይል እና የቁሳቁስ ዝግጁነት መጠናቀቁን ኮሚሽኑ አስታውቋል።
እስካሁን ባለው የምርጫ እንቅስቃሴ ፖስተር የቀደዱ ፣ የፓርቲዎች እጩ ተወዳዳሪዎችን ያስፈራሩ እና ሌሎች የምርጫ ስራዎችን በማወክ ወንጀል የተጠረጠሩ ሰዎችን በመያዝ 58 የምርመራ መዝገቦች ማደራጀቱንም የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ገልጿል።