ፖለቲካ
ጠ/ሚኒስትር ዐቢይ በተወዳሩበት የምርጫ ክልል በከፍተኛ የድምፅ ልዩነት አሸነፉ
ጠ/ሚ ዐቢይ በኦሮሚያ ክልል ጎማ ቁጥር 2 የምርጫ ክልል ነው ብልጽግናን ወክለው የተወዳሩት
በውጤቱም ጠ/ሚ ዐቢይ 76 ሺህ 892 ድምጽ ሲያገኙ፤ ተከታያቸው ደግሞ 236 ድምጽ አግኝተዋል።
የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ የተለያዩ የምርጫ ክልሎችን ውጤት ይፋ በማድረግ ላይ ይገኛል።
በኦሮሚያ ክልል ጎማ ቁጥር ሁለት የምርጫ ክልል የተወዳደሩት የብልጽግና የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዕጩ እና የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በከፍተኛ የድምጽ ልዩነት ማሸነፋቸውን ምርጫ ቦርድ ገልጿል፡፡
በምርጫ ክልሉ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትሕ፣ ሕብር እና ብልጽግና በምርጫ ክልሉ ዕጩዎችን አቅርበው ነበር።
በዚህም መሰረት የብልጽግና ዕጩ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ 76 ሺህ 892 ድምጽ ሲያገኙ፤ ተከታያቸው ደግሞ 236 ድምጽ አግኝተዋል።
በጎማ ቁጥር ሁለት ምርጫ ክልል አሸናፊው የብልጽግና ፓርቲ ሲሆን ዕጩው ደግሞ ዐቢይ አህመድ ናቸው፡፡
በዚህም መሰረት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የቀጣዩ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል መሆናቸው ተረጋግጧል ማለት ነው፡፡
በሕገ መንግስቱ አንቀጽ 73 መሰረት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት መካከል የሚመረጡ በመሆኑ ዶ/ር ዐቢይ ጠቅላይ ሚኒስትር ለመሆን የሚያስፈልገውን የፓርላማ አባልነት መስፈርትን ማሟላታቸው ተገልጿል።