በጦርነቱ ምክንያት ወደ ሱዳን ተሰደው የነበሩ ኢትዮጵያዊያን ወደ ሀገራቸው እየተመለሱ ነው ተባለ
የኢትዮጵያ እና ሱዳን ግንኙነት በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ሆኖም ቢሆን ዉጤታማ እንደሆነ ተገልጿል
በፌደራል መንግስት እና ህወሀት መካከል የሰላም ስምምነት መፈረሙን ተከትሎ ታጣቂዎችም እጅ እየሰጡ ነው ተብሏል
ጦርነቱ ምክንያት ወደ ሱዳን ተሰደው የነበሩ ኢትዮጵያዊያን ወደ ሀገራቸው እየተመለሱ መሆኑን በሱዳን ገዳሪፍ ግዛት የኢትዮጵያ ኮንሱል ጀነራል ተናገሩ።
በሰሜን ኢትዮጵያ በህወሃት እና የፌደራል መንግስት መካከል ጦርነት መጀመሩን ተከትሎ የኢትዮጵያ እና ሱዳን ግንኙነት ወደ መካረር አምርቶ እንደነበር ይታወሳል፡፡
የሁለቱ ሀገራት መሪዎች ቀስ በቀስ ባደረጓቸው ተከታታይ ግንኙነቶች እና ውይይቶች የኢትዮጵያ እና ሱዳን ዲፕሎማሲያዊ ወዳጅነት እየተሸሻለ መጥቷል፡፡
በሱዳን ገዳሪፍ ግዛት የኢትዮጵያ ኮንሱል ጀነራል አንተነህ ታሪኩ ለአል ዐይን አማርኛ እንደተናገሩት ኢትዮጵያ እና ሱዳን በችግር ጊዜ ውስጥም ሆነው ግንኙነታቸውን አለማቋረጣቸውን አንስተዋል፡፡
የጦርነቱ እንቅስቃሴ በሁለቱ ሀገራት ድንበር ላይም የነበረ ቢሆንም የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቱን ሊያቋርጥ የሚያስችል በይፋ የተዘጋ የጋራ ድንበር አለመኖሩንም ገልጸዋል፡፡
በጦርነቱ ምክንያት ለደህንነታቸው ፈርተውም ሆነ ከወንጀል ለማምለጥ ወደ ሱዳን የገቡ ኢትዮጵያዊያን ነበሩ የሚሉት ኮንሱል ጀነራሉ ሱዳን ኢትዮጵያዊያንን በማስጠለል ባለውለታችን ሀገር ናትም ብለዋል፡፡
የፌደራል መንግስት እና ህወሃት በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት መፈረማቸውን ተከትሎ የኢትዮጵያ እና ሱዳንም ግንኙነት አብሮ በፍጥነት እየተሸሻለ እንደሆነ የጠቀሱት ኮንሱል ጀነራሉ የተለየ የመንግስትን እገዛ ከሚጠይቁ ኢትዮጵያዊያን በስተቀር ወደ ሱዳን ተሰደው የነበሩ ዜጎች ወደ ኢትዮጵያ እየተመለሱ መሆኑንም አንስተዋል፡፡
ሱዳን የኢትዮጵያ ታጣቂዎች በግዛቷ ላይ ተደራጅተው ወደ ሀገራቸው ተመልሰው ጥቃት እንዲያደርሱ በማደራጀት እና ሌሎች ድጋፎችን አድርጋለች የሚል ክስ ብዙ ኢትዮጵያዊያን ሲያነሱ ቆይተዋል።
ነገርግን ኮንሱል ጀነራሉ “ የተለያዩ ወንጀሎችን ሰርተዋል የተባሉ ታጣቂዎች ወደ ሱዳን ሊገቡ ይችላሉ፣ ይሁንና የጦር መሳሪያ ታጥቆ በሱዳን ምድር የተንቀሳቀሰ እና ኢትዮጵያን መልሰው እንዲያጠቁ ድጋፍ የተደረገላቸው ታጣቂዎች የሉም፡፡” ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡
በወቅቱ የነበሩ ሁኔታዎች ሁለቱ ሀገራት በይፋ ወደ ጦርነት እንደገቡ አስመስሎ መረዳት ነበር፤ ነገር ግን ይህ ትክክል አይደለም፡፡ በተራ ሽፍትነት መልኩ ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ታጣቂዎች ግን ነበሩ ሲሉም አክለዋል፡፡
ሁለቱ ሀገራት ረጅም ርቀት ያለው የጋራ ድንበር መጋራታቸው ለግንኙነታቸው መልካም ቢሆንም ይህንን እድል ወደ ኢኮኖሚ ውህደት በሚወስዳቸው መልኩ በጋራ እያሰሩ እንዳልሆነ ጠቅሷል፡፡
የሁለቱ ሀገራት ረጅም የጋራ ድንበር ለህገወጥ ሰዎች ዝውውር፣ አደገኛ እጾች እና ሌሎች ህገወጥ እንቅስቃሴዎች እንዲኖሩ እድል ይፈጥራልም ብለዋል፡፡
ኮንሱል ጀነራሉ አክለውም የአንዱ ሀገር አለመረጋጋት ሌላውን ይጎዳል በሰሜን ኢትዮጵያ የነበረው ጦርነት ሱዳንን ጎድቷል፡፡ በሱዳንም የፖለቲካ አለመረጋጋቱ ኢትዮጵያን መጉዳቱ እንደማይቀር ጠቁመዋል፡፡
የሰላም ስምምነቱን ተከትሎ የሕዝብ ለህዝብ ግንኙነቱ እየጨመረ ነው የሚሉት አንተነህ የሰላም ስምምነቱን ተከትሎ በሁለቱ ሀገራት ድንበር ላይ የሚኖሩ የጋራ ህዝቦች ከጦርነቱ በፊት ወደ ነበረው የጋራ ንግድ እና ስራዎቻቸው ተመልሰዋል ብለዋል፡፡
እንዲሁም ወደ ሱዳን ገብተው የነበሩ ታጣቂዎችም ወደ ሀገራቸው በመግባት እጅ እየሰጡ ነው የሚሉት ጀነራሉ የጉምዝ፣ ቅማንት እና ሌሎችም ታጣቂዎችን ለአብነት አንስተዋል፡፡
የሰላም ስምምነቱ በአጭር ጊዜ ብዙ ነገሮችን ወደ ቀድሞ ሁኔታዎች እንዲመለሱ እያደረገ ነው የሚሉት አንተነህ በድንበር ላይ ይኖሩ የነበሩ የሁለቱ ሀገራት ህዝቦችን በነጻነት እንዲንቀሳቀሱ እድል ፈጥሯልም ብለዋል፡፡
የኢትዮ-ሱዳን የጋራ የየብስ ትራንስፖርት በኩል በመተማ-ጋላባት፣ በሁመራ በኩል ያለው የልጉዲ ዋና መተላለፊያ መስመሮች በጦርነቱ ወቅትም አለመዘጋታቸውን ያነሱት ኮንሱል ጀነራሉ ሰፊ ወታደራዊ እንቅስቃሴ በነበረባቸው መተላለፊያ መስመሮች ላይ ቢቀንስም የሑለቱ ሀገራት ህዝቦች ግን በጦርነቱም ጊዜ ግንኙነታቸው አለመቋረጡን አንስተዋል፡፡
የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቱ በጦርነቱም ወቅት ይደረግ ነበር የሚሉት ኮንሱል ጀነራሉ የሁለቱ ሀገራት ዩንቨርሲቲዎች፣ የጸጥታ ተቋማት ፣ ነጋዴዎች እና ኢንቨስተሮች በየጊዜው እየተገናኙ እና እየተወያዩ ይገኛሉም ብለዋል፡፡
ለአብነትም የገዚራ እና ባህር ዳር ዩንቨርሲቲዎች የጋራ ምርምር፣ የተማሪዎች ልውውጥ፣ ሳተላይት ቅርንጫፍ መክፈት እንዲሁም ገዳሪፍ እና ጎንደር ዩንቨርሲቲዎችም የጋራ ስምምነት በመፈጸም አብረው እየሰሩ ናቸው ተብሏል፡፡
የጸጥታ ተቋማትም በየጊዜው በመገናኘት ወንጀለኞችን መለዋወጥ፣ የጋራ ድንበር ላይ ጥበቃ ማድረግ እና ሌሎች የጸጥታ ስራዎችን እየሰሩ መሆናቸውን አቶ አንተነህ ጠቅሰዋል፡፡