ለሕወሓት የጦር መሳሪያ የማቅረብ ስራ የሚሰሩ በሰብዓዊነት ስም የሚንቀሳቀሱ ድርጅቶች መኖራቸው ተጠቆመ
የፕሬስ ሴክሬታሪያት ቢልለኔ እና ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ዶ/ር ጌዲዮን በትግራይ ክልል ጉዳይ ማብራሪያ ሰጥተዋል
የጠ/ሚ ጽ/ቤት ፕሬስ ሴክሬታሪያት ቢልለኔ ስዩም በመከላከያ ላይ የሚነሳውን ክስ “መሰረተ ቢስ” ብለዋል
በትግራይ ክልል ወቅታዊ ጉዳይ ዙሪያ የጠቅላይ ሚኒስቴር ጽ/ቤት ፕሬስ ሴክሬታሪያት ቢልለኔ ስዩም እና የፌዴራል ጠቅላይ አቃቤ ሕግ ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር) በኢትዮጵያ ለሚንቀሳቀሱ የውጭ መገናኛ ብዙሀን ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
መንግስት ከወራት በፊት በሰጠው ፈቃድ መሰረት እርዳታ ሰጭ ድርጅቶች በትግራይ ክልል ያለገደብ እየተንቀሳቀሱ እንደሚገኙ የገለጹት ቢልለኔ ፣ ይሁን እንጂ የደህንነት ችግር አለባቸው ተብለው በተለዩ ቦታዎች ላይ በመከላከያ መታገዝ እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል፡፡ የጸጥታ ችግር ባለባቸው ቦታዎች ላይ መድረስ ፈታኝ መሆኑንም ነው የጠቆሙት፡፡
ከዚህ በተቃራኒ የመንግስት ጦር የሰብዓዊ ድጋፍ እንዳይደርስ በመከልከል ላይ እንደሚገኝ የሚነገረው ወሬ ሀሰት መሆኑን አንስተዋል፡፡ ለአብነትም ገበሬዌች የእርሻ ስራዎቻቸውን እንዳያከናውኑ ስለመከልከላቸው በስፋት የተሰራጨውን መረጃ ለፖቲካ ፍጆታ የሚውል የሀሰት ወሬ ስለመሆኑ በማሳያነት አንስተዋል፡፡ ይህ ሆን ተብሎ “የሕወሓት አካላት የሚነዙት ወሬ ነው”ያሉት ቢልለኔ ፣ ዓላማውም የዓለም አቀፉን ማህበረሰብ እና የሚድያ አውታሮችን ቀልብ በመሳብ “ኢትዮጵያ ላይ ጫና መፍጠር ነው” ብለዋል፡፡
ስታስቡት ለምን ብሎ ነው መከላከያ ለ30 ዓመታት ያህል አብሮት በኖረው እና በአምበጣ ወረርሽኝ ወቅት አብሮት ሲለፋ በነበረው ገበሬ ላይ እንዲህ አይነት በደል የሚፈጽመው በማለትም ጠይቀዋል፡፡ በመሆኑም በመከላከያ ላይ የሚነሳውን ክስ “መሰረተ ቢስ ክስ ነው” በማለት አጣጥለዋል፡፡
የኤርትራ ወታደሮች መውጣትን በተመለከተ ፣ የመከላከያ ሚኒሰቴርን ሪፖርት በመጥቀስ የኤርትራን ጦር ከኢትዮጵያ የማስወጣት ሂደት መጀመሩን ፕሬስ ሴክሬታሪያቷ ገልጸዋል፡፡ በሁለቱ ሀገራት በተደረሰው ስምምነት መሰረትም የመውጣቱ ሂደት የሚቀጥል መሆኑንም ነው የጠቆሙት፡፡
ለሕወሓት የጦር መሳሪያ የማቅረብ ስራ የሚሰሩ በሰብዓዊነት ስም የሚንቀሳቀሱ ድርጅቶች መኖራቸውንም ነው ቢልለኔ የገለጹት፡፡ በዚህም ምክንያት የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት የፍተሻ ጣቢያዎችን አዘጋጅቶ የቁጥጥር ስራ በመስራት ላይ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ከዚህ ጉዳይ ጋር በተያያዘ የሚመለከተው አካል ሰፊ ማብራሪያ እንደሚሰጥበትም ቢልለኔ ከጋዜጠኞች ለተነሳላቸው ጥያቄ ማብራሪያ በሰጡበት ወቅት ገልጸዋል፡፡ የመንግስት ተልዕኮ የትግራይን ህዝብ መደገፍ ፣ የሰብዓዊ ድጋፎች እንዲደርሱ ማድረግ እና በክልሉ መረጋጋትን ማስፈን መሆኑን በመጥቀስ ፣ ህዝቡ በሕወሓት ምክንያት መጎዳት እንደሌለበት ተናግረዋል፡፡
ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ጌዲዮን ጢሞቲዎስ በበኩላቸው ከጦርነቱ ዝግጅት ጀምሮ በሕወሓት የተፈጸሙ ያሏቸውን የወንጀል ድርጊቶች እንዲሁም በጦርነቱ ወቅት በተዋጊኃይሎች የተፈጸሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን በተመለከተ አብራርተዋል፡፡
በትግራይ ክል ካለው ቀውስ ጋር በተያያዘ በኢትዮጵያ መንግስት ላይ በርካታ ዓለም አቀፍ ጫናዎች እያረፉ መሆኑ ይታወቃል፡፡ አሜሪካ ለግጭቱ ተጠያቂ ናቸው ባለቻቸው የቀድሞ እና ነባር የኢትዮጵያ ባለስልጣናት ላይ የቪዛ እገዳ መጣሏ ይታወቃል፡፡ እገዳው ፣ በኢትዮጵያ መንግስት በሽብርተኝነት የተፈረጀውን ፣ የሕወሓት አመራሮችንም የሚያካትት ነው፡፡