ከወራት በፊት በአክሱም በነበረው ውጊያ 99 ሰዎች መገደላቸው መረጋገጡን ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ገለፀ
ከአስገድዶ መድፈር ወንጀልን ጋር በተያያዘ 116 ተበዳዮች ለፖሊስ ቃላቸውን ሰጥተዋል ተብሏል
የምርመራው ሙሉ ውጤት ሲወጣ፣ ምን ያህል ንጹሃን እንደሞቱ ይፋ እንደሚደረግ ተገልጿል
በትግራይ ክልል አክሱም በነበረው ውጊያ 99 ሰዎች መሞታቸው እንደተረጋገጠ የፌዴራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ አስታወቀ፡፡
ምክትል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ፍቃዱ ጸጋ ዛሬ በሰጡት መግለጫ ፤ ተቋማቸው በትግራይ ክልል አክሱም ከተማ ህዳር 2013 ዓ.ም ተፈጽመዋል የተባሉ ወንጀሎችን የመመርመር ስራ በመሰራት ላይ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ይህንኑ ለማከናወንም ከፌዴራል ፖሊስ እና ከፌዴራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ የተውጣጣ የምርመራ ቡድን መቋቋሙንም ነው አቶ ፍቃዱ ያስታወቁት፡፡
በአክሱም ከተማ ሞቱ ስለተባሉ ሰዎች በተደረገ የማጣራት ስራ የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት የአክሱም ከተማ ከተቆጣጠረበት ዕለት ጀምሮ እስከ ሕዳር 18 ቀን 2013 ዓ.ም ስድስት (6) ሰዎች ሞታቸውን ተቋሙ ገልጿል፡፡ ሰዎቹ የሞቱት በጦርነቱ የሕወሓትን ቡድን ለማጥቃት የተተኮሰ መድፍ ኢላማውን በመሳቱ መሆኑ በምርመራ መረጋገጡን ነው ተቋሙ ይፋ ያደረገው፡፡ የተተኮሰው መድፍ ኢላማውን ስቶ በመኖሪያ ቤትና በአክሱም ዩኒቨርስቲ አካባቢ ወድቆ በመኖሪያ ስፍራው አራት፤ እንዲሁም በዩኒቨርሲቲው አካባቢ አንድ በድምሩ አምስት ሰዎች መሞታቸው መረጋገጡን ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ አስታውቋል፡፡ በክልሉ የታወጀውን አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በማስፈጸም ሂደት ውስጥ ከሰዓት ዕላፊ ጋር በተገናኘ በስራ ላይ ካሉ የፖሊስ አባላት ጋር በተፈጠረ እሰጥ አገባ ሌላ ተጨማሪ አንድ ሰው መገደሉንም ነው ተቋሙ ያስታወቀው፡፡
የፌዴራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ፣ የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ህዳር 18 ቀን 2013 ዓ.ም ለሌላ ግዳጅ ከተማውን ለቆ ሲወጣ የኤርትራ ሰራዊት ወደ አክሱም ማቅናቱን ማረጋገጡን ገልጿል፡፡ በወቅቱ በነበረው ውጊያ የደረሰውን ጉዳት ለማጣራት 95 ሰዎች የምስክርነት ቃል እንዲሰጡ መደረጉም ነው የተገለጸው፡፡
በውጊያውም 93 ሰዎች መሞታቸውም መረጋገጡን የጠቀሰው ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ፤ ሟቾቹ ወታደራዊ የደንብ ልብስ ባይለብሱም በአብዛኛው በጦርነቱ የተሳተፉ ሰዎች መሆናቸውም በምርመራው ፣መረጋገጡን አስታውቋል፡፡ በተደረገው ምርመራ በጦርነቱ ውስጥ ተሳትፎ ያልነበራቸው በመንገድ ላይ የነበሩ ንጹሀን መግደላቸው መረጋገጡም ነው የተጠቀሰው፡፡ የምርመራው ሙሉ ውጤት ሲወጣ፤ ምን ያህል ንጹሃን እንደሞቱ በቁጥር ተለይቶ እንደሚቀመጥ ምክትል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ፍቃዱ ጸጋ ገልጸዋል፡፡
የአስገድዶ መድፈር ወንጀልን በተመለከለተ በአጠቃላይ 116 ተበዳዮች ለፖሊስ ቃላቸውን መስጠታቸውንም አቶ ፍቃዱ አንስተዋል፡፡ በተከናወነው ምርመራም በወንጀሉ የተሳተፉ የፌዴራል ፖሊስ እና የመከላከያ ሰራዊት አባላት ተለይተው የፌደራል ፖሊስ አባላት ጉዳይ በክልሉ ዐቃቤ ሕግ እንዲመረመር ተደርጓል ብለዋል፡፡ በወንጀሉ የተሳተፉ የመከላከያ ሰራዊት አባላት በወታደራዊ ግዳጅ ላይ እያሉ የፈጸሙት ወንጀል በመሆኑ ጉዳዩ በወታደራዊ ፍርድ ቤት እንዲታይ ተላልፈው መሰጠታቸውም ነው በመግለጫቸው የጠቀሱት፡፡