በኢትዮጵያ በየአመቱ 23 ሺህ ሰዎች በኤች አይ ቪ ቫይረስ ይያዛሉ
የኢጥዮጵያ የኤች አይ ቪ ኤድስ መከላከልና መቆጣጠር ጽህፈት ቤት እንዳስታወቀዉ በሽታውን ለመቆጣጠርና ለመከላከል እየተሰራ ያለው ስራ በመቀዛቀዙ ምክንያት በሽታውን የመቆጣጠሩ ስራ አዝጋሚ ሆኗል፡፡
የኤች አይ ቪ የስርጭት ምጣኔ 0 ነጥብ 91 በመቶ ሲሆን ከ649 ሺህ በላይ የሚሆኑ ወገኖች ቫይረሱ በደማቸው እንደሚገኝ የ2019 አገራዊ የኤች አይ ቪ ስርጭት መረጃ ያሳያል።
የስርጭት ምጣኔውም ከክልል ክልል የሚለያይ ሲሆን በጋንቤላ፣ አዲስ አበባና ትግራይ የበሽታው ስርጭት መጠን ከሌሎቹ ክልሎች ከፍተኛ እና ወረርሽኝ በሚያስብል አሳሳቢ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ የጽህፈት ቤቱ የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ዳንኤል በትረ ለኢዜአ ገልጸዋል።
ዝቅተኛ ስርጭት ያለባቸው ክልሎች ደግሞ የሶማሌ፣ የኦሮሚያ እና የደቡብ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልሎች ናቸው፡፡
ከ10 አመታት በፊት ይደረግ የነበረው ትምህርትና ቅስቀሳ እየተቀዛቀዘ በመምጣቱ በየአመቱ አዲስ በቫይረሱ የሚያዙ ዜጎች ቁጥር እንዲጨምርና የበሽታው ስርጭት በተፈለገው ደረጃ እንዳይቀንስ አድርጎታልም ብለዋል።
ይህንን ችግር ለመፍታት ሁሉም የሚመለከታቸው አካላት የጋራ ርብርብ ማድረግ እንዳለባቸው ያስገነዘቡት አቶ ዳንኤል፤ የጥበብ ሰዎች፣ ሚዲያዎች እና ትምህርት ቤቶች ኤችአይቪ/ኤድስን ለለመከላከል በስፋት እንዲሰሩ ጥሪ አቅርበዋል።
የስራ ባህሪያቸው ለኤች አይ ቪ ኤድስ ተጋላጭ የሚያደርጋቸውን የህብረተሰብ ክፍሎች ግንዛቤ የማሳደግ ስራ መሰራት እንዳለበትም ተናግረዋል።
ክልሎች ላይ ያለው ስርጭት እንዲቀንስ ህብረተሰቡ ፣ የእምነት ተቋማት፣ ሚኒ-ሚዲያዎች ሰፊ ስራ መስራት እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።
የዘንድሮው የአለም የኤች አይ ቪ ቀን ማህበረሰብ የለውጥ አቅም ነው” በሚል መሪ ሃሳብ እየተዘከረ ነው።
ምንጭ፡- ኢዜአ