መተግበሪያው የቫይረሱ ታማሚዎች እና ምልክቱ የታየባቸው ሰዎች ባሉበት ቦታ ሆነው የሚመዘገቡበት ነው
የኮሮና ታማሚዎችና ምልክቱ የታየባቸው ሰዎች ባሉበት ቦታ ሆነው የሚመዘገቡበት መተግበሪያ በኢትዮጵያ ተሰራ
የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት በኮሮና ቫይረስ የተያዙ ታማሚዎችና ምልክቱ የሚታይባቸው ሰዎች ባሉበት ቦታ ሆነው የሚመዘገቡበት የሞባይልና የድረ ገጽ (ዌብ ሳይት) መተግበሪያ (አፕሊኬሽን) ሶፍትዌር መስራቱን አስታውቋል፡፡
የሞባይል መተግበሪያው በተንቀሳቃሽ የእጅ ስልክ ላይ በቀላሉ ሊጫን የሚችል ሲሆን ኢንቴርኔት ባለበት አካባቢ ሁሉ የሚሰራ ነው፡፡
በቫይረሱ የተያዙም ሆኑ ምልክቶቹ የታዩባቸው ሰዎች ይመዘገቡበታል፡፡ በአካባቢያቸው በቫይረሱ የተያዘም ሆነ የተጠረጠረ ሰው መኖሩን ሊገልጽ የሚችል መረጃም ያገኙበታል፡፡ የሰዎቹን ማንነትናያሉበትን ቦታ በተመለከተም ለዋና ማዕከሉ መረጃ ይሰጣል፡፡
መተግበሪያውን ለመጠቀም አንዴ የተመዘገቡ ሰዎች ኢንተርኔት በማይኖርባቸው ቦታዎች ጭምር ሊገለገሉ የሚችሉበትም ሲሆን በቫይረሱ ቢያዙ ከእነርሱ ጋር ንክኪ የነበራቸውን ሰዎችና የሄዱበትን ቦታ ሁሉ ለመለየት ያስችላል፡፡
ይህም በመንግስት በኩል የቫይረሱን ስርጭት ለመከላከል የሚደረገውን ያቀላል።
ሁለተኛው የድረ ገጽ መተግበሪያም ሰዎች ምልክቱ ከታየባቸው ጊዜ ጀምሮ በድረ ገጹ በመግባት የሚመዘገቡበትና በየጊዜው ያሉበትን ደረጃ የሚያሳውቁበት ነው፡፡
በተጨማሪም ኢንስቲትዩቱ ቫይረሱ በኢትዮጵያ ካለው አየር ንብረትና መልክዓምድር አንጻር ሊኖረው የሚችለውን ባህሪ ለማወቅ የሚያስችል ምርምርን እያካሄደ እንደሚገኝ አስታውቋል፡፡
ለዚህ የሚሆን ቡድን መቋቋሙን የገለጹት የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ሰሎሞን በላይ (ዶ/ር) በሀገራችን ያለውን አጋዥ የመተንፈሻ መሳሪያ (ቬንትሌተር) እጥረት ለመቅረፍ የሚያስችል ስራ እየተሰራ መሆኑን ጭምር ገልጸዋል፡፡
ዳይሬክተሩ በራሳቸው አንድ ቬንትሌተር ዲዛይን ማድረጋቸውን እና የዩኒቨርስቲ ተቋማት ለማስተማሪያነት የሚያገለገሉበት 8 ኢንች ቴሌስኮፕ እና 3ዲ ፕሪንተር መስራታቸውን የገለጹም ሲሆን መሳሪያዎቹን በብዛት የማምረት ስራ በቅርብ ጊዜ እንደሚጀመር ስለማብራራታቸውም ከኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡