ኮሮና እና ፌዴራሊዝም፡ምንና ምን ናቸው?
“በመንግስታቱ መካከል ተቃርኖ እና አለመግባባት ቢኖር እንዴት ሊፈታ ይችላል ስለሚለው ግን የተቀመጠ ነገር የለም”- ዘመልአክ አይተነው (ዶ/ር)
“ክልል መንግስታቱ ስርዓቱ ያጎናጸፋቸውን ስልጣን በወጉ እንዲያጣጥሙ እና ራስ ገዝነታቸውን እንዲያሳዩ ምቹ አጋጣሚን ፈጥሮላቸዋል”
ኮሮና እና ፌዴራሊዝም፡ምንና ምን ናቸው?
መላው ዓለምን ያዳረሰው የኮሮና ወረርሽኝ ወደ ኢትዮጵያም ገብቶ የፌዴራሉንም የክልሉንም መንግስት ፈጣን እና ያላሰለሰ ምላሽ እየጠየቀ ነው፡፡ የወረርሽኙን ስርጭት ለመግታትና ዜጎችን ከጉዳት ለመጠበቅም ከፍተኛ ጥረቶች በየደረጃው “መንግስታት” እየተደረጉ ነው፡፡ ይህም ጥረቶቹን ኢትዮጵያ ከምትከተለው የፌዴራል አወቃቀር የአስተዳደር ስርዓት አንጻር ለማየት፣ምን ዓይነት መስተጋብር እንዳላቸው ለማጤን፣ ስርዓቱን አዕማድ ሆነው ያቆሙት የፌዴራልና የክልል መንግስታት እንዴት ባለ መልኩ እየተንቀሳቀሱ እንደሆነ ለመፈተሽ እንዲሁም ስርዓቱ ወረርሽኙን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የሚያስችሉ ምን ዓይነት አጋጣሚዎችን ለመፍጠር እንደቻለ ለመመርመር እንዲል የሚሰጥ ነው፡፡ አል አይን አማርኛም ይህንኑ ታሳቢ አድርጎ ከባለሙያ ምክረ ኃሳብን ጠይቋል፡፡
የፌዴራሊዝም ተባባሪ ፕሮፌሰር የሆኑት ዘመላክ አይተነው (ዶ/ር) በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ መምህርና የዩኒቨርስቲው የፌዴራሊዝም ጥናት ተቋም ዋና ዳይሬክተር ናቸው፡፡ በዘርፉ በርካታ ጥናትና ምርምሮችን ያደረጉት ተባባሪ ፕሮፌሰሩ በቅርቡም ይህንኑ ጉዳይ የተመለከተና የኢትዮጵያን ወቅታዊ ሁኔታ የሚያስቃኝ መጣጥፍን በ’ፎረም ኦፍ ፌዴሬሽን‘ በኩል ለአንባቢ እንዲደርስ አድርገዋል፡፡ እኛም ኮሮናና ፌዴራሊዝም ምንና ምን እንደሆኑ በማጠየቅ ስለ ጉዳዩ ቅኝት ማድረጋችንን ጀምረናል፤ተከታተሉን፡፡
አል አይን ፡ ኮሮና እና ፌዴራሊዝም ምንና ምን ናቸው? ከዚህ ብንጀምር
ዘመልአክ አይተነው (ዶ/ር) ፡ ኮሮና የህዝብ ጤንነት (ፐብሊክ ሄልዝ) ጉዳይ ነው፡፡ በፌዴራል ስርዓት ውስጥ ደግሞ ይህ ጉዳይ የፌዴራልና የክልል መንግስታት ምን ስልጣን አላቸው በሚለው ይታያል፡፡ በህገ መንግስቱ በግልጽ እንደተቀመጠው ፌዴራል መንግስቱ ጉዳዩን የተመለከተ ፖሊሲ የማውጣት፣ ‘ስታንዳርዶችን’ የማስቀመጥ ስልጣን አለው፡፡ በዛ ላይ ደግሞ የተወሰኑ ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ የሚከፋፈሏቸው ነገሮችም አሉ፡፡ ስለዚህ እንደማንኛውም የጤና ጉዳይ ሁለቱም ኃላፊነት ይኖራቸዋል፡፡
ሁለተኛ (ጽሁፉም ላይ እንዳየኸው) ወረርሽኝ (ፓንደሚክ) የሚባለው ነገ ደግሞ ከሃገር ሃገር የሚሄድ ከሰዎች ጉዞ ድንበር ከማቋረጥ ጋር የሚያያዝ ነው፡፡ በዓለም የጤና ድርጅት ትርጓሜ መሰረት ‘ፓንደሚክ’ የተባለውም ለዚህ ነው፡፡ ስለዚህ ከሰዎች ወደ ኢትዮጵያ መግባትና አለመግባት ጋር የተያያዘ ነው ማለት ነው ራሱ የበሽታው መተላለፍ፡፡ ያ ማለት ደግሞ ሰዎች ወደ ሃገር ቤት ሲገቡ በበሽታው ምክንያት መግባት ትችላላችሁ ወይ ደግሞ መግባት አትችሉም ብሎ የመወሰን ስልጣን ያለው የትኛው የመንግስት አካል ነው የሚል ጥያቄ ያስነሳል፡፡ ይህ ግልጽ ነው የፌዴራል መንግስት ነው የሃገሪቷን መውጫና መግቢያ በሮች የሚቆጣጠረው፡፡ ከዛ ጋር በተያያዘም እንደዚሁ ወረርሽኙን የተመለከቱ የተወሰኑ ስልጣኖች አሉት፡፡ ሰዎች ወደ ሃገር ውስጥ ሲገቡ ምን ዓይነት ሁኔታዎችን አሟልተው መግባት አለባቸው ለምሳሌሙቀት ከመለካት አትገቡም እስከማለት ስልጣን አለው፡፡ ይህ ደግሞ በህገ መንግስቱ ከተከፋፈሉት ስልጣን ነው የሚመነጨው፡፡
ሶስተኛው ነገር ደግሞ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅን የማወጅ ነው፡፡ ክልሎችም እንደዚህ ዓይነት ወረርሽኝ ሲያጋጥም አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አውጆ የመቆጣጠር መብት አላቸው ፌዴራል መንግስቱም እንደዚሁ እንደሃገር የማወጅ ስልጣን አለው፡፡ እንደ ማንኛውም የጤና ጉዳይ እነዚህ እነዚህ ነገሮች ኮሮናንና ፌዴራሊዝሙን ያገናኛሉ፡፡
አል አይን ፡ የፌዴራል ስርዓት መከተሉ ወረርሽኙን በመከላከል እና በመቆጣጠር ሂደት ውስጥ ምን ምቹ ሁኔታዎች አሉት?
ዘመልአክ አይተነው (ዶ/ር) ፡ ምቹው ነገር ምንድነው እንደ ፍላጎታቸው ሊጠቀሙ የሚችሉበትን ዕድል (ፍሌክሲቢሊቲ) ይሰጣል፡፡ ኮሮናም ብቻ ባይሆን ሌሎች የህብረተሰብ ጤና ላይ የተጋረጡ አደጋዎች ሲያጋጥሙ ሁለቱም የመንግስት አካላት (ሌቭል ኦፍ ገቨርንመንት) በዚህ ጉዳይ ላይ ስልጣን ያላቸው መሆኑ “ፍሌክሲብል” እንዲሆኑ ያደርጋቸዋል፡፡ ፌዴራል መንግስቱ ’ችግሩ ያን ያህል የገዘፈ አይደለም‘ ብሎ የሚያስብ ከሆነና አንድ ክልል ‘የምመራውን በክልሌ ውስጥ ያለውን ሰው አደጋ ላይ መጣል የለብኝም’ ካለ የፌዴራሉን አካል ሳይጠብቅ ፍቃድም ሳያስፈልገው የራሱን እርምጃ እንዲወስድ ይፈቅድለታል፡፡
እንደ ሃገር የተደቀነ ስጋት፤ አደጋ ነው ካለ እና በሃገር አቀፍ ደረጃ እርምጃ መውሰድ ከፈለገ ደግሞ ለፌዴራል መንግስቱም ይፈቅድለታል እና የፌዴራል ስርዓቱ እንደ ችግሩ ስፋትና ጥልቀት የክልልም ሆነ የፌዴራሉ መንግስት የፈለገውን እንቅስቃሴ አድርጎ ነገሩን ነገሩን ለመቆጣጠር እንዲችል ያደርገዋል፡፡ “ፍሌክሲብል” ያደርገዋል፡፡ የተማከለ (ሴንትራላይዝድ) ቢሆን ኖሮ ሰዎች ቢታመሙም ቢወድቁም አንዳንድ መመሪያዎች ከፌዴራል መንግስቱ እስኪሰጡ ድረስ መጠበቅ ይኖርብሃል፡፡ እዚህ ጋ ግን ስልጣኑ ስላለህ ላለው ችግር ምላሽ መስጠት ትችላለህ፡፡ በዚያ መልኩ ጠቃሚ ነው፡፡
አል አይን ፡ ወረርሽኙ የፌዴራል ስርዓቱ ላይ ተጽዕኖ ሊያሳድር የሚችልበትስ አጋጣሚ አለ?
ዘመልአክ አይተነው (ዶ/ር) ፡ ትንሽ አሁን ሊያስፈራ የሚችለው ነገር ምናልባት ተቃርኖ ያለው ሊመስል የሚችል እርምጃን ከወሰዱ ፌዴራል መንግስቱ የሆነ ነገር ሲያዝ ክልሎች ሌላ እርምጃ ሊወስዱ ሲፈልጉ አሁን ደግሞ ትግራይ ከፌዴራል መንግስቱ ባለው እሰጣገባ እንደዚሁ ለወረርሽኙ ፖለቲካዊ ትርጓሜ ቢሰጥ እንዴት ሊፈታ ይችላል የሚለው ትልቅ ጉዳይ ነው፡፡ እዚህ ላይ ህገ መንግስቱ የሚሰጠን ግልጽ የሆነ ነገር የለም፡፡ ብዙ ጥያቄ የሚያስነሱ ጉዳዮችም አሉ፡፡ ተቃርኖ ቢኖር የሚያጋጥሙ ግጭቶች ቢኖሩ እንዴት ነው ሊፈታ የሚችለው የሚሉ ነገሮች ላይም ትንሽ ችግር አለ፡፡ በእንዲህ ዓይነት የችግር ወቅት ደግሞ እየተጓተትክ የህገ መንግስት ትርጓሜ አትጠይቅም ይሄ ይሄ የራሱን ችግር ይፈጥራል፡፡ ከዚያ ውጪ ግን በሁሉም የመንግስት ደረጃዎች “ፍሌክሲቢሊቲ” ይሰጣል፡፡
አል አይን ፡ ይህ ወረርሽኝ መምጣቱ ክልሎች የፌዴራል ስርዓቱ በሚፈቅድላቸው ልክ ስልጣናቸውን እንዲያሳዩ በወጉ እንዲያጣጥሙ ምቹ አጋጣሚ ፈጥሮላቸዋል ለማለት ይቻላል?
ዘመልአክ አይተነው (ዶ/ር) ፡ አዎ አየነው እኮ፡፡ የትግራይ ክልል የፌዴራል መንግስቱ አስቸኳይ ጊዜ ከማወጁ በፊት ነው ህገመንግስታዊ ስልጣኑን ተጠቅሞ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ያወጀው፡፡ ያ በግልጽ ስልጣንን በደንብ የማጣጣም ነገር ነው፡፡ ‘መብቴ ነው ህገ መንግስቱ ስልጣን ሰጥቶኛል ህዝቤን ከአደጋ እጠብቃለሁ ስለዚህ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አውጃለሁ ከፌዴራል መንግስቱ ምንም አቅጣጫ ሳልጠብቅ ቀጥታ ወደ ስራ መግባት እችላለሁ’ የሚለው አስተሳሰብ የመጣው ከስርዓቱ ከህገ መንግስታዊ የስልጣን ክፍፍሉ ጭምርም ነው፡፡
አል አይን ፡ ከፌዴራል መንግስቱ የስርዓቱ አካል ለሆኑ ክልሎች የሚሰጡ ድጋፎች የፍትሃዊነት ጥያቄ ሲነሳባቸው አደጉ በሚባሉት ሃገራት ጭምር እናያለን፡፡ በኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ የምንመለከታቸው ነገሮችም አሉ፡፡ እነዚህ ነገሮች ስርዓቱ የፈጠራቸው ወይስ ከዬት የመጡ ናቸው? ለምንስ ይነሳሉ?
ዘመልአክ አይተነው (ዶ/ር) ፡ እስካሁን ድረስ እንዴት እያስተባበሩት እንደሆነ ግልጽ የሆነ መረጃ የለኝም፡፡ የፌዴራል መንግስቱ ክልሎችን ለመርዳት ምን እያደረገ እንደሆነ እውነት ነው አውቃለሁ ፤ አሁን ለምሳሌ የትግራይ ክልል ‘የባጀት ድጎማ ይደረግልኝ ያላሰብኩት ነገር መጥቶ ብሬን ሁሉ እሱ ላይ ጨርሻለሁ’ የሚል ነገር እንዳሰማ አውቃለሁ፡፡ እንደዚሁም የሆነ ጊዜ ላይ ከፌዴራል መንግስቱ ለክልሎች የተወሰነ ዓይነት እርዳታ እንደሚሄድ ሲወራ ነበር መሰለኝ በተለይ ደግሞ ‘የብልጽግና’ ተብለው በሚታሰቡት (ክልሎች) ላይ፡፡
የሆነው ሆኖ ችግሩ ምንድነው የፌዴራል መንግስቱም ቢሆን ያን ያህል የረባ ሃብት የለውም፡፡ ነገርዬው እንዳልኩህ ዓለም አቀፋዊ ነው፡፡ ይሄንን ነገር ለመዋጋት ከሚያገለግሉት ራስን የሚጠበቂያ፣ የህክምና ባለሙያዎች ከሚጠቀሙባቸው ከፊትና አፍ መሸፈኛ ጭምብል (ማስክ) ጀምሮ ትንፈሳን እስከሚያግዙ መሳሪያዎች (ቬንትሌተር) ድረስ ውድድሩ እተካሄደ ያለው እንደ ኢትዮጵያ ባሉት ሃገሮች እና በሃብታሞቹ ሃገሮች ብቻ ሳይሆን ሃብታሞቹ ሃገሮች ራሳቸው እየተነጣጠቁ ነው ያሉት፡፡ ሃብቱ በጣም ትንሽ ነው ከጊዜ ወደ ጊዜም በጣም ውድ እየሆነ ማግኘቱ ከባድ እየሆነ ነው የመጣው፡፡ ስለዚህ በእርዳታ መልክ የሚመጣው አሁን ይሄ ከቻይና መጣ የሚባለው እርዳታ ካልሆነ በስተቀር የፌዴራሉም ሆነ የክልል መንግስታቱ ብዙም የሚችሉት (አፎርድ) የሚያርጉት ነገር እየሆነ አይደለም፡፡
ስለዚህ ዋነኛው ትኩረት (ፎከስ) መሆን ያለበት ነገር እንደመታደል ሆኖ እኛ እስካሁን ድረስ ወረርሽኙ ከቁጥጥር ውጭ አልሆነም 133 ሰዎች በቫይረሱ ተይዘዋል ተብሏል፡፡ አሁንም እሱው ላይ (ቁጥጥሩ ላይ) ማተኮሩ ነው የሚሻለው፡፡ ከቁጥጥር ውጭ ከሆነ ፌዴራል መንግስቱም ቢሆን ያን ያህል የረባ ስራ መስራት ይችላል ብዬ አላስብም ምክንያቱም ሃብቱ የለውም፤ዐቅም የለውም፡፡ አንዱ ከአንዱ ተሽሎ ሃብት ኖሮት ለአንዱ የሚሰጥና የሚከለክልበት ብዙም ጉዳይ አይደለም፡፡