የመመርመር ዐቅምን 7 ሺ ለማድረስ እየተሰራ ነው
እስከ 200 ሺ ሰው የሚይዙ ለይቶ ማቆያዎች ተዘጋጅተዋል
የቀውስ ጊዜ ፈጠራን አስመልክቶ በጠቅላይ ሚኒስትር አዘጋጅነት በተካሄደው የአዲስ ወግ የቪዲዮ ኮንፍረንስ ላይ የተሳተፉት የሰላም ሚኒስትሯ ሙፈሪያት ካሚል መንግስት ለችግሩ የሚመጥን ምላሽ ሰጥቷል ብለዋል፡፡
ህይወት የማዳን ጥረቱ ሰፊ ርብርብ የተደረገበት እና ውጤት የተገኘበት ነው ያሉት ሚኒስትሯ የምርመራ አቅም ማደግን፤የለይቶ ማቆያ ዝግጅትንና ግንዛቤ ፈጠራን በተመለከተ ሲሰሩ የነበሩ ስራዎችን በማሳያነት አንስተዋል፡፡
መንግስት በ1 ወር ከ15 ቀናት ውስጥ 24 ላቦራቶሪዎችን አቋቁሟል፡፡ ይህም ወረርሽኙ ወደ ሃገር ውስጥ በገባበት ጊዜ ወደ ውጭ ሃገራት ይላኩ የነበሩ የምርመራ ናሙናዎችን አስቀርቷል፡፡
በ24 ሰዓታት ውስጥ 4 ሺ 500 የደረሰውን የመመርመር አቅም ከ5ሺ እስከ 7ሺ ለማድረስ እየተሰራ ነው፡፡
“የችግሩን አሳሳቢነት አሻግሮ ተመልክቶ መጪውን ከግምት ያስገባ ዝግጅት ሲያደርግ ነበር” ያሉም ሲሆን የከፋ ችግር ቢገጥም እንኳን በሚል እስከ 200 ሺ ሰው ተለይቶ ሊቆይ የሚችልባቸው ማዕከላት ዝግጅት መደረጉን ገልጸዋል፡፡
ለዚህም በአጭር ጊዜ አንድ ሺ ሰው ማስተናገድ እንዲችል ሆኖ የተዘጋጀውን ሚሊኒዬም አዳራሽን ነው በማሳያነት ያስቀመጡት፡፡
“አስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ከህግና አዋጅነት ውጭ መሰረታዊ የሰው ልጆችን የመኖር መብት ለማገልገል የወጣ” መሆኑን የገለጹት ሚኒስትሯ ኢትዮጵያ ችግሩ የእኔ ብቻ ነው ሳትል በአህጉርና ዓለም አቀፍ ደረጃ ትልቅ ዲፕሎማሲያዊ ስኬት የተመዘገበበትን የመሪነት ሚና ተወጥታለች ብለዋል፡፡
ተቋማትንና ባለሃብቶችን በማስተባበር የተወጣችው የመሪነት ሚና ከፍ የሚያደርጋት ሲሉም ነው ያስቀመጡት፡፡
ችግሩ በሁሉም ላይ የተቃጣ በጋራ ሊመከት የሚገባው ነው በማለትም “ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከተለያዩ ሃገራት መሪዎች ጋር ወረርሽኙን በመከላከል ለመተባበር” እየተነጋገሩ እንደሆነም ተናግረዋል፡፡
ምጣኔ ሃብቱን ለመታደግና ክፍላተ ኢኮኖሚዎች እንዲያገግሙ ለማድረግ መንግስት ኃላፊነት የተሞላባቸውን በርካታ የፖሊሲ እርምጃዎች መውሰዱንም ነው የገለጹት፡፡
“ጥረቱ ህይወት የማዳን በመሆኑ ይሄ ሊሟላልን ይገባል የሚል ቅድመ ሁኔታን ሳያስቀምጡ ቅድሚያ ህይወት ለማዳን የተረባረቡ” የህክምና ባሙያዎችን፣የጸጥታ ኃይሎችን እና ወጣቱን ህብረተሰቡንም ጭምር አመስግነዋል፡፡