ዶ/ር ቴድሮስ ለዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተርነት ብቸኛ እጩ ሆነው መቅረባቸውን ተመድ ገለጸ
ዶ/ር ቴድሮስ ለሁለተኛ ጊዜ የዓለም ጤና ድርጅት እንዲመሩ 28 ሀገራት እጩ አድርገው መርጠዋቸዋል
የዶ/ር ቴድሮስ እጩነት በኢትዮጵያ መንግስት በኩል ድጋፍ ሳያገኝ ቀርቷል
የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተሩ ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም ለሁለተኛ ጊዜ የአለም ጤና ድርጅትን በዋና ዳይሬክትርነት እንዲመሩ ብቸኛ እጩ ሆነው መቅረባቸው ተመድ ገለጸ፡፡
ዶ/ር ቴድሮስ ለሚቀጥሉት አምስት ዓመታት የዓለም ጤና ድርጅትን እንዲመሩ እጩ ሆነው የቀረቡት የ28 ሀገራት ይሁንታ በማግኘታቸው ነው፡፡ለዶ/ር ቴድሮስ ድጋፋቸውን ከሰጡ ሀገራት መካከል ጀርመን እና ፈረንሳይ ከአውሮፓ እንዲሁም ቦትስዋና ፣ ኬንያ እና ሩዋንዳ ከአፍሪካ ይገኙበታል፡፡
በይፋዊ እጩነት ዝርዝር ውስጥ ብሪታንያ፣ቻይና፣ሩስያ እና ዩናይትድ ስቴትስ ድጋፍ በሰጡት ሀገራት ተርታ የሉበትም ተብሏል፡፡
የተመድ ኤጀንሲው ባወጣው መግለጫ "እጩ ይፋ የሚደረግበት ቀን እንደፈረንጆቹ ያለፈው መስከረም 23/2021 እንደመሆኑ ዶ/ር ቴድሮስ ብቸና እጩ እንደሆኑ ማሳወቅ እንችል ነበር ፤ ነገር ግን የዓለም ጤና ድርጅት ዘመቻ ለመቀነስ በሚል ጉዳዩን በሚስጥር ይዞት ቆይቷል"ብሏል፡፡
የተመድ ኤጀንሲው ቀደም ሲል ለአባል ሀገራት ሚስጥራዊ እጩዎች የሚገልጹበት የታሸጉ ኤንቨሎፖች ውስጥ ደብዳቤ መላኩንም ገልጸዋል፡፡
የኢትዮጵያ መንግስት የዶ/ር ቴድሮስ አድሀኖም እጩነት እንዳልተቀበለውም ነው ተመድ ያስታወቀው፡፡
ጉዳዩ አሳሳቢ ከመሆኑ የተነሳ የአፍሪካ ህብረት በዚህ ወር ባደረገው የመጨረሻ ጉባኤን ጨምሮ በሹመቱ ላይ ምንም ዓይነት ውይይት አለማድረጉም ጭምር ነው የዲፕሎማቲክ ምንጮች መረጃዎች የሚያመለክቱት፡፡
ዶክተር ቴድሮስ እስካሁንም እጩ የመሆን ፍላጎት ይኑራቸው አይኑራቸው ግልፅ ባያደርጉም፤ የአውሮፓም ሆነ የተወሰኑ የአፍሪካ ሀገራት ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖምን ለሁለተኛ ጊዜ የአለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር እንዲሆኑ ድጋፋቸውን ሲገልጹ መቆየታቸው የሚታወስ ነው፡፡
ሮይተርስ ስቴት ኒውስን ዋቢ በማድረግ ከወራት በፊት እንደዘገበው የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ቴድሮስ አድሃኖም የድርጅቱን ሀላፊ ሆነው ለቀጣይ አምስት አመታት ለምምራት በሚያስችላቸው የሁለተኛ ዙር ውድድር ለመሳተፍ ፍላጎት አላቸው ብሎ ነበር፡፡
ኢትዮጵያ በሰሜን ኢትዮጵያ በትግራይ ክልል በተፈጠረው ግጭት ምክንያት ቴዎድሮስን ለሁለተኛ ጊዜ ለመሾም ፈቃደኛ ባለመሆኗ፣ ሌሎች አገሮች ገብተው እንዲሳተፉ አስፈላጊ አድርጎታል።
የኢትዮጵያ መንግስት በትግራይ ግጭት ጉዳይ ዋና ዳይሬክተሩን ለቀድሞ ድርጅታቸው ህወሀት በመወገን የዲፕሎማሲ ድጋፍ አድረገዋል በማለት ሲከሳቸው ቆይቷል፡፡
ዶ/ር ቴድሮስ በበኩላቸው “እኔ ለማንም አልወግንም ውግንናየ ለሰላም ነው” በማለት በወቅቱ ምለሽ መስጠታቸው ይታወሳል፡፡በዚህ የተነሳ ዶ/ር ቴድሮስ እንደፈረንጆቹ ግንቦት 2022 በጀኔቭ በሚደረገው ምርጫ ከትውልድ ሀገራቸው ኢትዮጵያ ድጋፍ ሊያጡ እንደሚችሉ ይነሳል፡፡
በፈረንጆቹ በ2019 መገባደጃ ላይ አዲሱ የሳርስ ኮቭ ቱ (SARS-CoV-2) ቫይረስ በማዕከላዊ ቻይናዊቷ ውሃን ከተማ መከሰቱን ተከትሎ የዓለም የጤና ድርጅት ኮቪድ-19 ወረርሽኝን ለመታገል በሚያደርገው ትግል ዶ/ር ቴድሮስ ጎልተው ወጥተዋል፡፡
ዋና ዳይሬክተሩ ዋና ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም፤ ኮሮና ዓለም አቀፍ ወረርሺኝ ነው ተብሎ ከመፈረጁ በፊት በወርሀ ጥር 2020 ወደ ቻይና እቅንተው ከፕሬዝዳንት ዢ ጂንፒንግ ጋር በትብብር ለመስራት በሚያስችሏቸው ጉዳዮች መምከራቸው የሚታወስ ነው፡፡
ይሁን እንጅ ይህ አካሄድ በቀድሞ የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ አልተወደደላቸውም ነበር፡፡
ዶናልድ ትራምፕ የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተሩ ዶ/ር ቴድሮስን "አፍቃሬ-ቻይና" ናቸው በሚል ክስ፤ አሜሪካ በድርጀቱ የነበራትን ሚና እንድትገታ ውሳኔ አሳልፈው እንደነበርም የሚታወስ ነው፡፡ ምንም እንኳ አሁን ላይ የትራምፕ ውሳኔ በአዲሱ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ጆ-ባይደን ቢቀለበስም፡፡
ዶ/ር ቴድሮስ የዓለም ጤና ድርጅትን እየመሩ ያሉ የመጀመርያው በታሪክ አፍሪካዊ መሆናቸው ይታወቃል፡፡
ዶ/ር ቴድሮስ የኢትዮጵያ ጤና ጥበቃ ሚኒስትር በነበሩበት ወቅት የወባ በሽታ፣ ኤች አይ ስረጭት እንዲሁም የእናቶች እና ጨቅላ ህፃናት ሞት እንዲቀንስ በሰሩት ስራ እውቅና እንደተሰጣቸው ይታወሳል፡፡