የራስ ገዝ ዩኒቨርስቲዎች “የትምህርት ክፍያ” በህዝብ ተወካዮች ም/ቤት አባላት ጥያቄ ተነሳበት
የእንደራሴዎች ም/ቤት የራስ ገዝ ዩኒቨርስቲዎች እንዲቋቋሙ ወሰነ
በቀጣዮቹ ሁለት ዓመታት ስምንት ዪኒቨርስቲዎች ራስ ገዝ እንደሚሆኑ ትምህርት ሚንስቴር አስታውቋል
የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የራስ ገዝ ዩንቨርስቲዎች እንዲቋቋሙ ተወሰነ
መንግስት “ተቋማዊ ነጻነትን” ለማምጣት ራስ ገዝ ዩኒቨርስቲዎች እንዲቋቋሙ ወስኗል።
የሚንስትሮች ም/ቤት የራስ ገዝ ዩኒቨርስቲዎች ረቂቅ አዋጅ አጽድቆ ለህዝብ ተወካዮች ም/ቤት የመራው ሲሆን በም/ቤቱ አባላትም ጉልህ “የፍትኃዊነት” ጥያቄ ተነስቶበታል።
ራስ ገዝ ዩኒቨርስቲዎቹ የአካዳሚ፣ የአስተዳደር፣ የፋይናንስ እና የሰው ሀብት አስተዳደራቸው ላይ ነጻነት እንደሚኖራቸው ተነግሯል።
ራስ ገዝ ሆነው የሚቋቋሙት ዩኒቨርስቲዎች የሀብት ምንጫቸውን ለማስፋት ለትምህርት የሚጠይቁት ክፍያ አሁን በነጻ እየተሰጠ ያለውን ትምህርት ይገድባል የሚል ስጋት ተሰንዝሯል።
በተለይም በዝቅተኛ ገቢ የሚተዳደሩ ዜጎችን በማግለል፤ የትምህርት ፍትኃዊነት ያሳጣል ያሉት አባላቱ ጊዜውን ያዋጀ ነው ወይ ሲሉ ጠይቀዋል።
“አዋጁ ላይ በግልጽ እንደተመለከተው መንግስት በሂደት ለከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚሰጠውን ፈንድ በመቀነስ ተማሪዎችና ወላጆቻቸው ወጪዎቻቸውን እንዲሸፍኑ ታሳቢ ያደረገ ነው። [ይህን ለማድረግ] አሁን ማህበራዊና ኢኮኖሚያ መደላድሎች አሉ ወይ? የአርሶ አደር ልጆች፤ በዝቅተኛ ገቢ የሚተዳደሩ ተማሪች ለክፍያው አቅም አላቸው?” ሲሉ የም/ቤቱ አባል ደሳለኝ ጫኔ (ዶ/ር) ጠይቀዋል።
ተስፋነሽ ተፈራ የተባሉ የም/ቤት አባልም መክፈል የሚችለውን ብቻ በማስተማር አቅም የሌላቸውን ማስቀረት አይሆንም ወይ? በማለት ተቋማቱ ከግል ዩኒቨርስቲዎች ጋር የሚኖራቸውን መሰረታዊ ልዩነት ጠይቀዋል።
የራሳቸውን ልምድ በማንሳት በአቅም ምክንያት በራስ ገዝ ዩኒቨርስቲዎች መማር እንደማይችሉ ያነሱት ሌላ የም/ቤት አባል አዳሙ ቀንዓ (ረ/ፕ) ገቢራዊነቱ እምብዛም እንዳልተዋጠላቸው ገልጸዋል። “የሀብታሞች ት/ቤት” ሲሉ ለራስ ገዝ ዩኒቨርስቲዎች ስያሜ የሰጡት አባሉ፤ ወክለነዋል ላሉት ሰፊው ህዝብ የትምህርት እድል መገደቡ አሳሳቢ ነው ብለዋል።
“የደሀ፣ የገበሬ፣ የመንግስት ሰራተኛ ልጆች ት/ቤት አይገቡም ማለት ነው። ትምህርት ቁሳዊ እየተደረገ ነው። ትምህርት በገንዘብ እየሆነ ነው። ከሀገር አንጻር ጥሩ እድል ሊኖረው ይችላል። ግን የኛ ማህበረሰብ ፍላጎት ይሄ ነው ወይ? ድሮ በዋጋ መጋራት ድጎማ ነበር። ይሄኛው ሌላ ቀውስ ይዞ አይመጣም? በደሀና በሀብታም መካከል ያለውን የጥቅም ግጭት ሊያሰፋ ይችላል የሚል ሀሳብ አለኝ” ብለዋል።
ከመንግስት “ብሎክ ግራንት” ይመደብላቸዋል የተባሉት ራስ ገዝ ዩኒቨርስቲዎቹ፤ በጀቱ ፍትኃዊነትንና አካታችነትን ማረጋገጥ ታሳቢ እንደሚያደርግ ተጠቅሷል።
የመንግስት ተጠሪ ሚንስትር ተስፋዬ በልጅጌ የትምህርት ጥራትን ለማሻሻል እየተሰሩ ካሉ ስራዎች ውስጥ የራስ ገዝ ዩኒቨርስቲዎች መቋቋም አንዱ ነው ብለዋል።
መነሻው ዩኒቨርስቲዎች ናቸው ያሉት ተጠሪው፤ ተቋማቱ “በተተበተበ የቢሮክራት አስተዳደር” ተልዕኳችንን ለመፈጸም እንቸገራለን በማለታቸው እርምጃው መምጣቱን ጠቅሰዋል።
ዓላማው የተቋማቱ “ነጻነትና ውድድር” መሆኑን በማንሳትም፤ “ምሰሶው” የመንግስትን በጀት ለመቀነስ ሳይሆን ዩኒቨርስቲዎች ተጨማሪ ሀብት እንዲያመነጩ ማድረግ ነው ሲሉ ለተነሱ ጥያቄዎች ላይ አስተያየት ሰጥተዋል።
ለዝርዝር እይታ ረቂቅ አዋጁ የተመራለት የሰው ሀብት ልማት፣ ስራ ስምሪትና ቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ስጋቶችን እንደሚጋራቸው ገልጿል። የኮሚቴው ሰብሳቢ ነገሪ ሌንጮ (ዶ/ር) “ስጋቶቹ እንዲቀረፉ አስፈላጊ ማሻሻያዎች ተደርገዋል” ብለዋል።
“ተማሪዎቻችን ላይ በር እንዲዘጋ አንፈልግም። የተነሳው የሀብታም ዩኒቨርስቲ ይሆናል፣ የደሀ ተማሪዎች ሊማሩ አይችሉም የሚለውን ቀደም ብለን ውይይት አድርገን እንደዚህ እንዳይሆን አስፈለጊ ማሻሻያ አድርገናል። በትክክል አይተን ተስተካክሏል” በማለት አብራርተዋል።
ም/ቤቱ በአራት ተቃውሞና በ13 ድምጸ ተአቅቦ የራስ ገዝ ዩኒቨርስቲዎችን ለማቋቋም የወጣውን አዋጅ አጽድቋል።
የመጀመሪያው ራስ ገዝ ዩኒቨርስቲ ይሆናል የተባለው አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የመዋቅር፣ የሰው ኃይል፣ የፕሮግራም፣ የተማሪ አቀባበልና የወጪ አሸፋፈን ስርዓት ላይ ጥናት ማድረጉ ታውቋል።