እስካሁን 5 ነጥብ 6 ሚልዮን ኩንታል ወደ አገር ውስጥ ገብቷል
የግብርና ሚኒስቴር በየዓመቱ እያጠና በሚያቀርበው የሀገሪቱ የአፈር ማዳበሪያ ፍላጎት መሰረት የኢትዮጵያ የግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን ከተቋቋመበት ከ2008 ዓ.ም. ጀምሮ ዓለም አቀፍ ጨረታ እያወጣ የማዳበሪያ ግዥ በመፈጸም ላይ ይገኛል።
በዚህ መሰረት ኮርፖሬሽኑ ለ2015/16 የሰብል ዘመን ከውጭ ከሚያስገባው 12 ሚሊዮን 875 ሺህ 520 ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ውስጥ እስካሁን 5 ሚሊዮን 675 ሺህ 520 ኩንታል ኤን ፒ ኤስ፣ ኤን ፒ ኤስ ቦሮን እና ዩሪያ ጂቡቲ ወደብ ደርሷል።
ከዚህ መጠን ውስጥ እስከ ግንቦት 11/2015 ዓ.ም. ድረስ 5 ሚሊዮን 571 ሺህ 72 ኩንታል (98%) ወደ ሀገር ውስጥ ተጓጉዞ ለአርሶ አደር ዩኒየኖች እየተሰራጨ ነው።
በተጨማሪም ግንቦት 14 እና ግንቦት 23/2015 ዓ.ም. እያንዳንዳቸው 600 ሺህ ከንታል ኤን ፒ ኤስ ቦሮን የአፈር ማዳበሪያ በአጠቃላይ 1 ሚሊዮን 200 ሺህ ኩንታል የጫኑ ሁለት መርከቦች ጂቡቲ ወደብ እንደሚደርሱ ይጠበቃል።