አዲሱ የዩንቨርሲቲ ተማሪዎች መመደቢያ መስፈርት ምን ምን ይዟል?
ትምህርት ሚኒስቴር የዩንቨርሲቲ ተማሪዎችን መመደቢያ መስፈርቶችን ይፋ አድርጓል
በምደባ መስፈርቶቹ ከውጤት እና ዩንቨርሲቲ ምርጫዎች በተጨማሪ የወሊድ እና መንትዮችን ጉዳዮች ሳይቀር አካቷል
አዲሱ የዩንቨርሲቲ ተማሪዎች መመደቢያ መስፈርት ምን ምን ይዟል?
ትምህርት ሚኒስቴር በ2015 የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ብሄራዊ ፈተና ወስደው ያለፉ ተማሪዎች የዩኒቨርሲቲ ምደባ አሰራር ዙሪያ ማብራሪያ ሰጥቷል፡፡
ሚኒስቴሩ ወደ ዩንቨርሲቲ ተማሪዎችን ሲመድብ ከሚከተላቸው መስፈርቶች መካከል የተማሪዎች ውጤት፣ ምርጫ፣ ውጤት፣ የዩንቨርሲቲ ምርጫ እና ያላቸው ፕሮግራም፣ጾታ እና ሌሎችንም ጉዳዮች ማካተቱን አስታውቋል፡፡
እንደ ሚኒስቴሩ ማብራሪያ 1000 የሚሆኑ ከፍተኛ ውጤት ያስመዘገቡ ተማሪዎች በመጀመሪያ የዩኒቨርስቲ እና የትምህርት መስክ ምርጫቸው ይመደባሉ፡፡
ሌላኛው የምደባ መስፈርት ውጤት ሲሆን የተሻለ ውጤት ያስመዘገቡ ተማሪዎች ሌሎች ተፈጻሚ የሚሆኑ ህግና ደንቦችን ባልጣሰ መልኩ ምርጫቸው ተጠብቆ ምደባው ይከናወናል ተብሏል፡፡
ሌላኛው የምደባ መስፈርት የዩኒቨርሲቲ ምርጫ ሲሆን የምደባ ስርዓቱ በተማሪዎች የተመረጡ 46 ዩኒቨርሲቲዎች ያላቸውን የቅበላ አቅም ታሳቢ ባደረገ መልኩ እንደሚካሄድም ተገልጿል፡፡
የ2015 የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና ልናውቃቸው የሚገባ እውነታዎች ምንድናቸው?
በተማሪዎች የተመረጡ ተቋማት ያላቸው የትምህርት ፕሮግራሞች አራተኛው የዩንቨርሲቲ ተማሪዎች መመደቢያ መስፈርት ሲሆን በተማሪዎች የተመረጡ የትምህርት ፕሮግራሞች እና የተመረጡት ዩኒቨርሲቲዎች ያላቸውን የትምህርት ፕሮግራም መሰረት ያደረገ እንዲሆን ተደርጓል ተብሏል፡፡
ጾታ የውጤት እና ትምህርት ቤት ተዋጽኦ ሲሆን በተቋማት የጾታ ተዋጽኦን ውጤትን እና የትምህርት ቤቶችን ስብጥር በጠበቀ እንደሚመደቡ ተገልጿል፡፡
የወሊድ ጉዳይ ፣ ህክምና ፣ የአካል ጉዳት እና ተመሳሳይ ጾታ ያላቸው የመንትዮች ጉዳዮች ተጨማሪ የመመደቢያ መስፈርት ሲሆን ማስረጃዎችን መሰረት በማድረግ ተማሪዎች በተመደቡበት ዩኒቨርሲቲ ለመቀጠል የሚቸገሩ ከሆነ ትክክለኛ ለውጥና ድጋፍ ይደረግላቸዋል ተብሏል፡፡
በማይገባቸው ዩንቨርሲቲ እና የተለየ ጥቅም ለማግኘት ሲሉ ሀሰተኛ የህክምና ማስረጃ የሚያቀርቡ ተማሪ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ከምደባ ውጭ እንደሚደረጉ ትምህርት ሚኒስቴር አስጠንቅቋል፡፡