“ሀገራት በኢትዮጵያ ግዛታዊ አንድነት ላይ ጽኑ አቋም እንዲይዙ ተደርጓል” አምባሳደር ዲና ሙፍቲ
“ም/ጠ/ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን በአፍሪካና በአውሮፓ ያደረጓቸው ጉብኝቶች ትልቅ ፋይዳ ነበራቸው”
በትግራይ በሚካሔደው የሕግ ማስከበር ተግባር ዙሪያ ስኬታማ የዲፕሎማሲ ሥራ መሰራቱ ተገልጿል
“ሀገራት በኢትዮጵያ ግዛታዊ አንድነት ላይ ጽኑ አቋም እንዲይዙ ተደርጓል” አምባሳደር ዲና ሙፍቲ
ኢትዮጵያ በትግራይ ክልል የጀመረችው ሕግ የማስከበር ሥራን በተመለከተ ዓለም ትክክለኛውን ምስል እንድይዝ መሰራቱን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
የሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ በትግራይ ክልል የተካሄደው ሕግ የማስከበር ስራ ምንነትና በስኬት መጠናቀቁንም ጭምር ዓለም እንዲያውቀው የሚያስችል የውጭ ግንኙነት ሥራ መሰራቱን ገልጸዋል፡፡ በሁለት ሳምንት አንድ ጊዜ በሚሰጠው መደበኛ መግለጫ ላይ የሕግ ማስከበር ተልዕኮን በተመለከተ በተሰራው የዲፕሎማሲ ሥራ ሀገራትና ዓለም አቀፍ ተቋማት ከኢትዮጵያ ጎን እንዲሰለፉ መደረጉን ቃል አቀባዩ አስታውቀዋል፡፡
ለዚህም ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን በአፍሪካና በአውሮፓ ያደረጓቸው ጉብኝቶች ትልቅ ፋይዳ ነበራቸው ብለዋል፡፡ ኢትዮጵያን በውጭ ሀገራት የሚወክሉ ዲፕሎማቶችም የሕግ ማስከበር ሥራውን ዓለም በትክክል እንዲረዳው በማድረግ በኩል ስኬታማ ሥራ መከናወኑን ይፋ አድርገዋል፡፡ ይሁንና አንዳንድ ዲፕሎማቶች አሁንም ብዙ መስራት እንዳለባቸው ገልጸው “ገና ተኝተው ያሉም አሉ” ብለዋል፡፡
በሰሜን የሀገሪቱ ክፍል ላለፉት ሳምንታት የተካሄደው የህግ ማስከበር ዘመቻ በተሳካ ሁኔታ መጠናቀቁን የገለጹት አምባሳደር ዲና ፣ ሀገራትና ዓለም አቀፍ ተቋማት የኢትጵያን ግዛታዊ አንድነት እንደሚያከብሩ እና ለዚህም ሕግ የማስከበሩን ሥራ ትክክል እንደሆነ ተረድተዋል ብለዋል፡፡
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አቶ ደመቀ መኮንን ሕግ የማስከበር ሥራው ከተጠናቀቀ በኋላም ከሩሲያው ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌ ላቭሮቭ ጋር መወያየጣቸውን የገለጹት አምባሳደር ዲና ሞስኮ የህግ ማስከበር ዘመቻው የኢትዮጵያን ግዛታዊ አንድነት ለመጠበቅ የተደረገ እንደሆነ አቋም መያዟንም ገልጸዋል፡፡