በጠ/ሚኒስትሩ የተቋቋመ ግብረ ኃይል የመተከል ዞንን የፀጥታ ማስከበር ስራ ተረከበ
ግብረ ኃይሉ ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎችና የመከላከያ ሠራዊት አመራሮች የተካተቱበት ነው
የንጹሃንን ሕይወት በማጥፋት የተሳተፉ ተጠርጣሪዎችን የማደን ስራ መቀጠሉን ሌ/ጄኔራል አስራት ዴኔሮ ገልጸዋል
በጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አሕመድ የተቋቋመው ግብረ ኃይል የመተከል ዞንን የፀጥታ ማስከበር ስራ መረከቡን ሌ/ጄኔራል አስራት ዴኔሮ አስታወቁ።
በጠቅላይ ሚኒስትሩ የተቋቋመውና ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎችና የመከላከያ ሠራዊት አመራሮች የተካተቱበት ግብረ ኃይል በዞኑ የሕግ የበላይነትን የማረጋገጥ ስራውን ሙሉ በሙሉ ጀምሯል።
የፀጥታ ኃይሉን የሚመሩት ሌ/ጄኔራል አስራት ዴኔሮ እንደገለጹት፣ የንጹሃንን ሕይወት በማጥፋት ወንጀል የተሳተፉ ተጠርጣሪዎችን የማደን ስራው ቀጥሏል።
“በወንጀሉ የተሳተፉ ተጠርጣሪዎች በአጭር ጊዜ የሕግ ተጠያቂ ይሆናሉ” ሲሉም ተናግረዋል።
ችግሩን ከመሰረቱ ለመፍታት በአሁኑ ወቅት በየደረጃው ከሚገኙ የማኅበረሰብ አባላትና አመራሮች ጋር ውይይት እየተካሄደ ሲሆን ወንጀለኞቹን በመለየት ለሕግ የማቅረቡ ስራም እንደሚቀጥል ሌ/ጄኔራሉ ተናግረዋል።
ከዚህ ጎን ለጎን የተፈናቀሉትን መልሶ የማቋቋምና የሕዝቡን የዕለት ተዕለት ኑሮ ቀድሞ ወደነበረበት የመመለስ ስራ እንደሚሰራም መግለጻአውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
ሌ/ጄኔራል አስራት ዴኔሮ “በመተከል ዞን የተጀመረው የሕግ የበላይነትን የማረጋገጥ ተልዕኮ በአጭር ጊዜ ይጠናቀቃል” ብለዋል።