ምዕራባዊያንና ዓለም አቀፍ ተቋማት በኢትዮጵያ ላይ ጫና ለማሳደር እየሞከሩ ነው ሲል መንግስት ሲከስ ቆይቷል
ኢትዮጵያውያን የውጭ ጣልቃ ገብነትን በመቃወም በተለያዩ የአዲስ አበባ ጎዳናዎች ድምጻቸውን አሰሙ፡፡
ኢትዮጵያውያኑ በተለያዩ የከተማዋ ስፍራዎች “እጃችሁን ከኢትዮጵያ ላይ አንሱ” በሚል መሪ ኃሳብ በአገሪቱ የውስጥ ጉዳይ የውጭ ጣልቃ ገብነትን በመቃወም ድመጻቸውን አሰምተዋል፡፡
“እጃችሁን ከኢትዮጵያ ላይ አንሱ”፣ “ምዕራባውያን በኢትዮጵያ ጉዳይ ጣልቃ እየገቡ የሚያሳድሩት ተጽዕኖ የአገርን ሉዓላዊነት የሚጥስ ነው”፣ “ግድቡ የኔ ነው” የሚሉና መሰል መልዕክቶችን በመያዝም ነው በተሸከርካሪዎች ድምጽ ጭምር በመታጀብ ተቋውሟቸውን የገለፁት።
ድምጽ የማሰማት መርሃ ግብሩ አዲስ አበባ በሚገኘው ከአሜሪካ ኤምባሲ ውጪ ተቃውሞ እንደሚካሄድ ቀደም ብሎ የተገለጸ ቢሆንም በዛሬው ዕለት ይህ ሊከናወን አልቻለም፡፡
ምክንያቱም ኤምባሲዎቹ ዝግ በመሆናቸው እንደሆነ ከመርሃ ግብሩ አስተባባሪዎች አንዱ የሆኑት አቶ ዐብይ ታደለ ለአል-ዐይን አማርኛ ተናግረዋል፡፡
ኮሚቴው ኤምባሲዎቹን ቀጠሮ እንዲሰጠው መጠየቁንና ቀጠሮውን በሚሰጣቸው ጊዜ ደብዳቤውን በአካል እንደሚያቀርቡ አስተባባሪው አክለዋል።
የአሜሪካ ኤምባሲ ትናንት ባወጣው መግለጫ በማኅበራዊ የትስስር ገጾች በኤምባሲው አካባቢ ተቃውሞ ሊኖር እንደሚችል በመግለጽ አርብ መሥሪያ ቤቱ ዝግ መሆኑን ማስታወቁ ይታወሳል።
ምዕራባዊያንና ዓለም አቀፍ ተቋማት በኢትዮጵያ ላይ ጫና ለማሳደር እየሞከሩ ነው ሲል የኢትዮጵያ መንግሥት ቅሬታውን ሲያሰማ ቆይቷል።
ከዚሁ ጋር በተያያዘ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድን ጨምሮ ሌሎች የአገሪቱ ባለሥልጣናት በተለያዩ መድረኮች ላይ ምዕራባዊያን በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ውስጥ ጣልቃ ለመግባት እየሞከሩ መሆናቸውን፤ ነገር ግን ይህ ተቀባይነት እንደሌለው ሲናገሩ ተደምጠዋል።
ይህ “ብሔራዊ ክብር በሕብር” የተሰኘው በታዋቂ ሰዎች የተዘጋጀው እንቅስቃሴም ዜጎች የውጭ አገር መንግሥታት በኢትዮጵያ ጉዳይ ውስጥ ጣልቃ ለመግባት እያደረጉ ነው ያሉትን ጥረት ለመቃወም የተዘጋጀ መሆኑ ተገልጿል።