የሕዳሴ ግድብ ለዘንድሮ የታቀደውን 4.9 ቢ.ኪ.ሜ. ዉሃ ይዟል
የግድቡን የመጀመሪያ ዙር የዉሃ ሙሌት በመጠናቀቁ ከፍተኛ ባለስልጣናት በትዊተራቸው ደስታቸውን ገልጸዋል
ስለ ግድቡ ሊያውቋቸው የሚገቡ ዋና ዋና ቁጥራዊ መረጃዎች የትኞቹ ናቸው?
የሕዳሴ ግድብ ለዘንድሮ የታቀደውን 4.9 ቢ.ኪ.ሜ. ዉሃ ይዟል
የግድቡ የመሰረት ድንጋይ ተጥሎ ግንባታው ከተጀመረ ከ 9 ዓመታት በኋላ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ፣ምንም እንኳን ከሚጠበቀው ጊዜ ቢዘገይም ፣ በአዲስ መልክ በታቀደው መሰረት ዉሃ መያዝ ጀምሯል፡፡
የግድቡን የመጀመሪያ ዙር የዉሃ ሙሌት በተመለከተ የግድቡ ዋነኛ ተደራዳሪዎች እና የኢትዮጵያ ከፍተኛ ባለስልጣናት በመግለጫ እና በትዊተራቸው የብስራት ዜናዎችን አስፍረዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ የግድቡ የመጀመሪያ ዙር ሙሌት በስኬት መጠናቀቁን ለመገናኛ ብዙኃን በጽሁፍ በላኩት መግለጫ አብስረዋል፡፡ በትዊተር ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሁፍ ደግሞ በአፍሪካ ሕብረት አደራዳሪነት ትናንት ሐምሌ 14 ቀን 2012 ዓ.ም የተካሔደው ዉይይት ስኬታማ እንደነበር ገልጸው በግድቡ ውሃ አሞላል ዙሪያ ቴክኒካዊ ውይይቶችን ቀጥሎ ለማካሄድ የጋራ መግባባት ላይ ለደረሱት የሱዳን እና የግብጽ መሪዎች አድናቆታቸውን ገልጸዋል።
የዉጭ ጉዳይ ሚኒስትር ገዱ አንዳርጋቸው በትዊተራቸው “የድል ብስራት! ዐባይ ወንዝ ነበር ፤ ተገርቶ ወንዝም ሀይቅም ሆነ። ከእንግዲህ በወንዝነቱ ይፈሳል። በሀይቅነቱ ኢትዮጵያ ለፈለገችው ልማት ሁሉ ለመዋል እጅ ሰጥቷል። እውነትም ዐባይ የእኛ ሆነ!!” ብለው ጽፈዋል፡፡
“እንኳን ደስ አለን” በሚል በትዊተራቸው ጽሁፋቸውን የጀመሩት የዉሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ዶ/ር ኢ/ር ስለሺ በቀለ ደግሞ “ሐምሌ 12/2012 ዓም ከምሽቱ 4 ሰዓት ላይ የህዳሴ ግድብ የመጀመሪያ ዓመት ሙሊት ተሳክቷል: ውሃው የሚያስፈልገውን 4.9ቢ.ኪዩቢክ ሜትር በመያዝ ከግድቡ አናት ላይ ፈሷል ይህም የተሳካው ወደታችኛው ተፋሰስ የሚሄደው ውሃ ሳይቋረጥ ነው” ብለዋል፡፡
አሁን በግድቡ የተያዘው ዉሃ በቀጣዩ ዓመት (2013 ዓ.ም ወይም በአውሮፓውያኑ በምንገኝበት 2020) በ 2 ተርባይኖች 750 ሜ.ዋ. የኤሌክትሪክ ኃይል ለማመንጨት ያስችላል ተብሏል፡፡