የህዳሴው ግድብ ድርድር በህጋዊ ጉዳዮች ላይ ስምምነት ሳይደረስ መጠናቀቁ ተገለጸ
በቴክኒክ ጉዳዮች 95 በመቶ መግባባት መደረሱን የሱዳን የዉሃና መስኖ ሚኒስቴር ገልጿል
መግባባት ያልተደረሰባቸው የህግ ጉዳዮች ለፖለቲካ ውሳኔ ለሦስቱ ሀገራት መሪዎች መላካቸውን ሱዳን አስታወቀች
የህዳሴው ግድብ ድርድር በህጋዊ ጉዳዮች ላይ ስምምነት ሳይደረስ መጠናቀቁ ተገለጸ
በሱዳን አነሳሽነት በታላቁ የህዳሴ ግድብ ዙሪያ በኢትዮጵያ ፣ ሱዳን እና ግብፅ የውሃ ሚነስትሮች መካከል በቪዲዮ ኮንፈረንስ ሲካሄድ በነበረው ድርድር በአብዛኛው ጉዳዮች ላይ መግባባት ቢደረስም በህጋዊ ጉዳዮች ላይ ግን መግባባት እንዳልተቻለ የሱዳን የውሃና መስኖ ሚኒስቴር ገልጿል። ሚኒስትሩ ያሰር አባስ (ፕ/ር) ምሽት በሰጡት መግለጫ ውይይቱ በብዙ ጉዳዮች ላይ በተለይም በቴክኒክ ጉዳይ 95 በመቶ መግባባት የተደረሰበት ነው ብለዋል።
ሦስቱ ሀገራት በህግ ጉዳዮች ከፍተኛ ልዩነት እንዳላቸው በመጠቆም ፣ መግባባት ያልተደረሰባቸው የህግ ጉዳዮች በመሪዎች ደረጃ ፖለቲካዊ እልባት እንዲሰጥባቸው ጉዳዩ ወደ ሦስቱ ሀገራት መሪዎች መላኩንም ሚኒስትሩ ገልጸዋል።
የሱዳን ፍላጎት ውይይቱ በግድቡ የውሃ ሙሌት እና አስተዳደር ላይ ያተኩር የሚል ሲሆን በዚህ ጉዳይ መግባባት ተደርሷል ነው ያሉት። ይሁንና መግባባት ያልተደረሰባቸው የተለያዩ ህጋዊ ጉዳዮች ያሉ ሲሆን ከነዚህም በኢትዮጵያ የተነሳው ከ10 ዓመት በኋላ የውሀ ክፍፍል እናድርግ የሚለው ሲጠቀስ በግብፅ በኩል ደግሞ ከዚህ ቀደም የተደረሱ ስምምነቶች መፍረስ የለባቸውም እና ወደ ዋሽንግተን ድርድር ልንመለስ ይገባል የሚሉት ይገኛሉ።
ግብፅ ከዚህም በተጨማሪ እንደ ዓለም አቀፍ ተቋማት ፣ አሜሪካ እና የአውሮፓ ህብረት ያሉ ምስክሮች ባሉበት እንዲፈርሙ ትፈለልጋለችም ነው ያሉት ፕሮፌሰር ያሰር አባስ።
ጉዳዩን ግብፅ ወደ ተባበሩት መንግስታት የጸጥታው ምክር ቤት የመውሰድ አቋም እና ፍላጎት ቢኖራትም ሱዳን ልዩነቱ ወደ ጸጥታው ም/ቤት ሳያመራ በሦስትዮሽ ድርድር ሊፈታ ይችላል ባይ ነች ፤ የኢትዮጵያም አቋም ይሄው መሆኑ ይታወቃል።
የዉሃ ሙሌት እና አስተዳደርን በተመለከተ ሱዳን እና ግብፅ አስገዳጅ ስምምነት ይፈረም የሚል አቋም ሲይዙ ኢትዮጵያ ደግሞ መፈረም ያለበት አስገዳጅ ሳይሆን መሪ ስምምነት መሆን አለበት የሚል አቋም እንደያዘች የሱዳን የውሃና መስኖ ሚኒስትሩ ያሰር አባስ (ፕ/ር) በመግለጫቸው አብራርተዋል።
ሱዳን እና ግብፅ ከኢትዮጵያ በተቃራኒ ስምምነት ሳይደረስ የግድቡ የዉሃ ሙሌት መጀመር የለበትም በሚለው የጋራ አቋማቸውን እንደጸኑ መቀጠላቸውንም ሚኒስትሩ ገልጸዋል።
የሶስቱ ሀገራት መሪዎች ባቀረቡላቸው የህግ ጉዳዮች ላይ ፖለቲካዊ ውሳኔ ከሰጡ ኋላ ድርድሩ ከቀጠለ የተሻለ ውጤት ሊኖረው እንደሚችል ሱዳን እንደምታምን ፕሮፌሰር አባስ ተናግረዋል።
ሚኒስትሩ መግለጫውን የሰጡት የሱዳን ብሔራዊ የሽግግር ም/ቤት ምክትል ፕሬዘዳንት ሌተናል ጄነራል መሐመድ ሃምዳን ደገሎ በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ለመምከር ዛሬ አዲስ አበባ ከገቡ ከጥቂት ሰዓታት በኋላ ነው።
ግብፅ እና ኢትዮጵያ መወነጃጀላቸውን እንደቀጠሉ ናቸው።
ግብፅ ግድቡ ከአባይ ወንዝ የማገኘውን የዉሃ መጠን ይቀንስብኛል፤ ይሔም ኢኮኖሚያዊ ፖለቲካዊ እና ማህበራዊ ቀውስ ያስከትልብኛል የሚል እምነት ሲኖራት ኢትዮጵያ ደግሞ ግብፅና ሱዳን ላይ ጉልህ ጉዳት በማያደርስ መልኩ የተፈጥሮ ሀብቴን እጠቀማለሁ የሚል ጽኑ አቋም ይዛ ግድቡን መገንባቷን ቀጥላለች፡፡