አንዳንድ ኤምባሲዎች ዶላር መመንዘርና የኢትዮጵያን ሀብት እየዘረፉ ማሸሽ ቋሚ ሥራቸው አድርገውታል- ጠ/ሚ ዐቢይ
በተያዘው በጀት አመት 1.5 ትሪሊየን ብር ከግብር ለመሰብሰብ መታቀዱን ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ ተናገሩ
ጠቅላይ ሚንስትሩ በምክር ቤት እየሰጡት ባለው ማብራርያ፤ ለደመወዝ ጭማሪ 91 ቢሊየን ብር ተመድቧል ብለዋል
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 6ኛ ዙር 4ኛ ዓመት 3ኛ መደበኛ ጉባኤውን እያካሄደ ይገኛል፡፡
በጉባኤው የምክር ቤት አባላቱ ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮችን የተመለከቱ ጥያቄዎችን አንስተዋል፡፡
መንግስት በቅርቡ ካደረገው የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ጋር ተያይዞ በኢኮኖሚው እና በዝቅተኛ ገቢ በሚኖረው ማህበረሰብ ውስጥ እየፈጠረ ይገኛል በተባሉ ተጽዕኖዎች ዙርያ ጥያቄ ተነስቷል፡፡
የምርት እጥረት ፣ ለውጭ ገበያ የሚቀርቡ ግብአቶች ፣ የዋጋ ንረት እና የስራ እድልን የተመለከቱ ጉዳዮች በተጨማሪ ከተነሱ ጥያቄዎች መካከል ናቸው፡፡
በምክር ቤት አባላቱ ለተነሱ ጥያቄዎች ማብራርያ የሰጡት ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) ከዋጋ ንረት ጋር ተያይዞ መሻሻሎች እየታዩ መሆናቸውን ባለፈው ዓመታት 26 በመቶ የነበረው የዋጋ ንረት ዘንድሮ 17 በመቶ ወርዷል ብለዋል፡፡
ጠቅላይ ሚንስትሩ በ2017 በጀት አመት 8.4 በመቶ አጠቃላይ ሀገራዊ ምርት እድገት ለማስመዝገብ እቅድ ተይዟል ብለው በዘርፍ በዘርፍ እድገት ይመዘገብባቸዋል የተባሉ የኢኮኖሚ ዘርፎችን ጠቅሰዋል፡፡
ከነዚህ መካከል ግብርና ቀዳሚው ሲሆን ዘርፉ በ2017 በጀት አመት 6.1 በመቶ እድገት ያስመዘግባል ተብሎ እንደሚጠበቅ ተጠቅሷል፡፡
ጥጥ ፣ ሰብል እና ሆሊቲካቸርን ጨምሮ 30 ሚሊየን ሄክታር መሬት በምርት በመሸፈን 1.4 ቢሊየን ኩንታል ምርት ይጠበቃል ያሉት ጠቅላይ ሚንስትሩ ከሰብል ምርት ብቻ 6.6 በመቶ እድገት እንደሚኖር ነው የጠቆሙት፡፡
ሀገሪቱ ወደ ውጭ ልካ ከፍተኛ ገቢ ከምታገኝብቻው ዘርፎች መካከል አንዱ የሆነው ቡና ባለፈው አመት 1ሚሊየን ኩንታል ምርት የተገኝ ሲሆን በዚህም 1.4 ቢሊየን ዶላር ገቢ ተገኝቷል ነው የተባለው፡፡
በዚህ አመት ይመረታል ተብሎ ከሚጠበቀው ከ450 ሺህ -500 ሺህ ቶን ቡና 2 ቢሊየን ዶላር ገቢ ለማግኝት እቅድ ተይዟል፡፡
ስንዴን በተመለከተ መስኖን ጨምሮ በክረምት እና በጋ ወራት 8.2 ሚሊየን ሄክታር መሬት በስንዴ በመሸፈን 300 ሚሊየን ኩንታል ምርት እንደሚጠበቅ ጠቅላይ ሚንስትር አብይ በማብራርያቸው አመላክተዋል፡፡
ከግብርና ዘርፍ ቀጥሎ የአገልግሎት እና የኢንዱስትሪ ዘርፎች ከፍተኛ ተስፋ ተጥሎባቸዋል ያሉት ጠቅላይ ሚንስትሩ ኢንዱስትሪ 12.8 በመቶ የአገልግሎት ዘርፉ ደግሞ 7.1 በመቶ እድገት እንደሚያስመዘግብ ጠቅሰዋል፡፡
ከገቢ እና ታክስ አሰባሰብ ጋር በተያያዘ ባነሱት ሀሳብ ኢትዮጵያ ከአጠቃላይ ሀገራዊ ምርቷ ግብር 8.5 በመቶ እንዲሸፍን እቅድ መያዙን ነው የተናገሩት፡፡
በዚህ መሰረትም በ2017 አመት ከፌደራል 900 ቢሊየን ከክልሎች 600 ቢሊየን በአመቱ በአጠቃላይ 1.5 ትሪሊየን ብር ገቢ ለመሰብሰብ መንግስት እየተንቀሳቀሰ ነው ብለዋል፡፡ ባለፉት 3ወራትም 180 ቢሊየን ብር ገቢ መሰብሰቡን አክለው ገልጸዋል፡፡
በተጨማሪም የብሔራዊ ባንክ መጠባበቂያ ተቀማጭ 161 በመቶ ፣ የግል ባንኮች ደግሞ 29 በመቶ እድገት እንደታየበት ተነግሯል፡፡
የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያውን ተከትሎ ባላፉት ሶስት ወራት ከወጪ ንግድ 1 ነጥብ 5 ቢሊዮን ዶላር ገቢ መገኘቱንም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል።
በዚህ አፈጻጸም ከቀጠልን በበጀት ዓመቱ መጠናቀቂያ ላይ ከ5 ቢሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፤ ይህ ካለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጻር የ1 ቢሊዮን ዶላር ጭማሪ አለው ብለዋል።
በተለይ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው በወርቅ ምርት ወጪ ንግድ ላይ ትልቅ ለውጥ አምጥቷል ያሉ ሲሆን፤ ባለፉት ሶስት ወራት ከወርቅ ወጪ ንግድ 500 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ተገኝቷል፤ ይህም የወርቅ ምርት ምን ያህል ለህገ ወጥ ንግድ ተጋልጦ እንደነበር የሚያሳይ ነው ብለዋል።
ባንኮች ባለፉት ሶስት ወራት ከማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው ጋር በተያያዘ 652 ሚሊየን ዶላር ገዝተው አንድ ቢሊየን ዶላር መሸጣቸው ታውቋል፡፡
ከውጭ ወደ ሀገር ውስጥ የሚላከው ገንዘብ (ሬሚታንስ) 24 በመቶ ማደጉ ሲገለጽ አጠቃላይ በሀገሪቱ የሚንቀሳቀሱ ባንኮች ሀብት 3.5 ትሪሊየን ብር እንደረሰ ነው ጠቅላይ ሚንስትር አብይ የተናገሩት።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አያይዘውም፤ በህጋዊና በጥቁር ገበያው መካከል ያለው የምንዛሬ ልዩነት እንዲጠብ የተሰራው ሥራ ወጣታማ ሆኖ ልዩነቱ ወደ አምስት በመቶ መውረዱን ተናግረዋል።
ይሁንና አሁንም የውጭ ምንዛሬ ገበያው ላይ የሚደረጉ አሻጥሮች እንዳልተቀረፉ የጠቆሙት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ በተለይ ኤምባሲዎችን በዚህ ውስጥ ጠቅሰዋል።
አንዳንድ ኤምባሲዎች ዶላር መመንዘርና የኢትዮጵያን ሀብት እየዘረፉ ማሸሽ ቋሚ ሥራቸው አድርገውታል ሲሉም ወቅሰዋል።
እነዚህን ኤምባሲዎች እስካሁን በትዕግሥት እያለፍናቸው ነው፣ ነገር ግን ከዚህ ድርጊታቸው ካልተቆጠቡ ርምጃ ይወሰድባቸዋል ብለዋል።
ይሁንና ጠቅላይ ሚኒስትሩ በንግግራቸው የኢትዮጵያን ሀብት ይዘርፋሉ ያሏቸውን ኤምባሲዎች በስም አልጠቀሱም።
በሌላ በኩል በሩብ አመቱ ከእርዳታ እና ብድር 3.4 ቢሊየን ዶላር እንደተገኝ እና በአጠቃላይ በማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው 27 ቢሊየን ዶላር ወደ ኢትዮጵያ እንደሚመጣ ይጠበቃል ተብሏል፡፡