በቻይና ሀገር የሚመረተው የቮልስ ዋገን የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ በጊዜያዊነት ወደ ኢትዮጵያ እንዳይገባ ታግዷል
ኢትዮጵያ የቮልስዋግን ኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ ወደ ሀገሯ እንዳይገባ አገደች፡፡
መንግስት የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች በስፋት እንዲመረቱ፣ እንዲገጣጠሙና ወደ ሀገር ውስጥ እንዲገቡ የተለያዩ ማበረታቻዎችን ለይቶ ተግባራዊ በማድረግ ላይ ነኝ ብሏል፡፡
የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ ኢንቨስትመንትንና አስመጪዎችን የሚያበረታታ እንዲሁም ህብረተሰቡን ተጠቃሚ የሚያደርግ የታክስ ማሻሻያ ተግባራዊ መደረጉንም መንግስት ገልጿል፡፡
ወደ ኢትዮጵያ ከሚገቡ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች መካከል በቻይና ሀገር ተገጣጥሞ ወደ ኢትዮጲያ እየገባ የሚገኘው ቮልስ ዋገን የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ ህጋዊ የሆነ ፍቃድ የሌለው መሆኑ ተገልጿል፡፡
ቮልስዋገን ኩባንያ በጀርመን ኢንባሲ በኩል ለትራንሰፖርት እና ሎጅስቲክስ ሚኒስቴር በጻፈው ደብዳቤ አንዳሳወቀው በቻይና የሚገጣጠመውና ወደ ኢትዮጵያ እየገባ ያለው የኩባንያው ምርቶች ህጋዊ አለመሆናቸውን ማሳወቁ ተገልጿል፡፡
በዚህ መሰረትም ቻይና ሀገር የሚመረተው የቮልስ ዋገን የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ ከኩባንያው ህጋዊ ፈቃድ ያለው መሆኑ እስኪረጋገጥ ድረስ በጊዜያዊነት ወደ ኢትዮጵያ እንዳይገባ መታገዱን ሚኒስቴሩ አስታውቋል፡፡
ኢትዮጵያ በቀጣዮቹ አስር ዓመታት ውስጥ ከ150 ሺህ በላይ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን ወደ ሀገር ውስጥ ለማስገባት ማቀዷ ይታወሳል፡፡
ከውጭ የሚገቡም ሆነ በሀገር ውስጥ የሚመረቱ የኤሌክትሪክ የህዝብ ማመላለሻ ተሽከርካሪዎች፣ የቤት አውቶሞቢሎች እና የእቃ መጫኛ ተሽከርካሪዎች ላይ የዝቅተኛ ቀረጥ ታሪፍ የሚጣልባቸው ሲሆን ከተጨማሪ እሴት ታክስ፣ ከኤክሳይዝ ታክስና ከሱር ታክስ ነፃ እንዲሆኑ ተደርጓል፡፡
የታክስ ማሻሻያው አላማ በአገራችን በከፍተኛ ፍጥነት እያደገ የመጣውን የተሽከርካሪዎች ቁጥር በፖሊሲ ማዕቀፍ ከአካባቢ ደህንነት ጋር የሚስማማ ለማድረግ፣ በህብረተሰቡ ጤና ላይ ጉዳት የማያስከትል፣ በአየር ንብረትና በብዝሃ ህይወት ላይ ተጽእኖ የማያሳርፍ እና ታዳሽ የኃይል ምንጮችን በአግባቡ የሚጠቀም የማጓጓዣ ሥርዓት ተግባራዊ ለማድረግ ሲሆን የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን በተመጣጣኝ ዋጋ ለህብረተሰቡ እንዲቀርቡ ለማስቻልም ነው ተብሏል፡፡
ይህንንም ዓላማ ለማሳካት ወደ ሀገር ውስጥ የሚገቡ ተሽከርካሪዎች ላይ ክትትል በማድረግና የህጋዊነት ማረጋገጫ መረጃዎችን የማጥራት ስራም በከፍተኛ ጥንቃቄ እየሰራ መሆኑን መንግስት አስታውቋል፡፡