የአውሮፓ ህብረት የሃማስ የፖለቲካ መሪን በሽብርተኞች ዝርዝሩ አካተተ
የህብረቱ አባል ሀገራት በያህያ ሲንዋር የተመዘገበ ሃብት እንዳይንቀሳቀስ ለማገድም ተስማምተዋል
ያህያ ሲንዋር እስራኤል በጋዛ አጥብቃ ከምትፈልጋቸው የሃማስ መሪዎች መካከል አንዱ ነው
የአውሮፓ ህብረት አባል ሀገራት የሃማስ የፖለቲካ መሪ ያህያ ሲንዋርን በህብረቱ የሽብርተኞች ዝርዝር ውስጥ ማካተታቸው ተገለጸ።
የህብረቱ አባል ሀገራት በያህያ ሲንዋር ስም የተመዘገበ ሃብት እንዳያንቀሳቅስ ለማገድና በግለሰቡ ስም ምንም አይነት እንቅስቃሴዎች እንዳይካሄዱም ነው ስምምነት ላይ የደረሱት።
ሃማስ ጥቅምት 7 በእስራኤል ላይ የፈጸመውን ድንገተኛ ጥቃት በማቀነባበር ትልቅ ድርሻ አለው ተብሎ የሚታመነው ሲንዋር እስራኤል በጋዛ አጥብቃ የምትፈልጋቸው የሃማስ መሪዎች መካከል ይጠቀሳል።
የፍልስጤሙን ቡድን የፖለቲካ እና ወታደራዊ ክንፍ በማቀናጀት እና በመምራት ስሙ ጎልቶ የሚነሳው ያህያ ሲንዋር በፈረንጆቹ 2017 ነው በጋዛ የሃማስ መሪ ሆኖ የተመረጠው።
እስራኤል ደጋግማ ያሰረችው ሲንዋር በ2011 በተካሄደ የእስረኞች ልውውጥ መፈታቱንም የዩሮኒውስ ዘገባ ያወሳል።
በአደባባይ ተቃውሞዎች የማይጠፋው ያህያ ሲንዋርም የእስራኤልን ጥቃት ፍራቻ ማንኛውንም የኤሌክትሮኒክስ መሳሪያዎች መጠቀም ካቆመ አመታት ተቆጥረዋል።
አሜሪካ ይህን ግለሰብ በ2015 በአለማቀፍ ሽብርተኞች ዝርዝር ውስጥ ያካተተችው ሲሆን፥ ብሪታንያም ከአንድ ወር በፊት ሽብርተኛ ብላ የተለያዩ ማዕቀቦችን ጥላበታለች።
ያህያ ሲንዋር የእስራኤልና ሃማስ ጦርነት ከተጀመረ ወዲህ በአውሮፓ ህብረት በግለሰብ ደረጃ ማዕቀብ የተጣለበት ሶስተኛው የሃማስ ከፍተኛ አመራር ነው።
የህብረቱ አባል ሀገራት የሃማስ ወታደራዊ ክንፍ አዛዡ መሀመድ ዴይፍ እና ምክትሉን ማርዋን ኢሳ በሽብርተኝነት መፈረጃቸው የሚታወስ ነው።
የአውሮፓ ህብረት፣ አሜሪካ እና ሌሎች ምዕራባውያን ሃገራት ሃማስን በሽብርተኛ ቡድንነት መፈረጃቸው ይታወቃል።