በቤሩት የተገደሉት የሃማስ መሪው ሳሌህ አል አሩሪ ማን ነበሩ?
እስራኤል በቱርክና በሊባኖስ በስደት ያሳለፉትን ሳሌል አል አሩሪ ከ2014 ጀምሮ ስታድን ቆይታለች
አሜሪካ ግለሰቡ ያለበትን ለጠቆመኝ 5 ሚሊየን ዶላር ጉርሻ እሰጣለሁ ማለቷ ይታወሳል
ሃማስ የፖለቲካ ቢሮ ምክትል መሪው ሳሌህ አል አሩሪ በቤሩት መገደላቸውን አረጋግጧል።
የፍልስጤሙ ቡድን “አስቀያሚ ግድያ” በሚል የገለጸውን የድሮን ጥቃት እስራኤል እንደፈጸመችው አስታውቋል (ምንም እንኳን ቴል አቪቭ ማረጋገጥም ሆነ ማስተባበል ባትፈልግም)።
በሃማስ ቢሮ ላይ በተፈጸመው ጥቃት ከአል አሩሪ በተጨማሪ ስድስት ሰዎች ህይወታቸው ማለፉን የሊባኖስ መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።
ሳሌህ አል አሩሪ ማን ነበሩ?
በእስራኤል እስርቤቶች ለ15 አመታት የታሰሩት ሳሌህ አል አሩሪ ከእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ተደጋጋሚ የግድያ ዛቻ ደርሷቸዋል። ቴል አቪቭ አል አሩሪን ለአስር አመት ገደማ ስትፈልጋቸው ቆይታለች።
በፈረንጆቹ 2014 በዌስትባንክ ሶስት እስራኤላውያን ታዳጊዎች የታገቱበትንና የተገደሉበትን ዘመቻ መርተዋል በሚል ነው ቴል አቪቭ በአይነ ቁራኛ ስትመለከት የቆየችው።
የ57 አመቱ አል አሩሪ በወቅቱ የሃማስ ወታደራዊ ክንፍ (አልቃሳም ብርጌድ) የፈጸመውን ተግባር ማወደሳቸውን ኒውዮርክ ታይምስ ያወሳል።
ከተገደሉት ታዳጊዎች ውስጥ አንደኛው ትውልደ እስራኤላዊ አሜሪካዊ መሆኑን ተከትሎም ዋሽንግተን አል አሩሪን በ2015 በአለማቀፍ ሽብርተኝነት ፈርጃ ያለበትን ለጠቆመኝ የ5 ሚሊየን ዶላር ጉርሻ አዘጋጅቻለሁ ማለቷም አይዘነጋም።
አል አሩሪ በቱርክ በስደት ላይ ሆነው ከዌስትባንኩ ጥቃት ባሻገር የፍልስጤም አስተዳደር ፕሬዝዳንቱን ሙሀመድ አባስ ከስልጣን ለማንሳት ሴራ ሲጎነጉኑ ነበር የሚል ወቀሳም በእስራኤል በኩል ይቀርብባቸዋል።
ሳሌህ አል አሩሪ በ2017 የሃማስ የፖለቲካ ቢሮ ምክትል መሪ ሃላፊ ሆነው ከተመረጡ በኋላም የእስራኤል ክትትል ይበልጥ ተጠናክሯል።
ከሃማስ የጋዛ መሪ ያህያ ሲንዋር ጋር ጥብቅ ወዳጅነት እንዳለላቸው የሚነገርላቸው አል አሩሪ የሃማስ እና ሄዝቦላህን ግንኙነት በማጠናከር ትልቅ ድርሻ ነበራቸው።
ከቱርክ ወደ ሊባኖስ ካመሩ በኋላም “በሄዝቦላህ የሃማስ አምባሳደር” የሚል ተቀጽላ ተሰጥቷቸዋል።
አል አሩሪ የሃማስ የፖለቲካ ቢሮ ምክትል ሃላፊ ሆነው እንደተመረጡ ያቀኑት ወደ ኢራን ነው። በዚህም ቴህራን ለፍልስጤሙ ቡድን ድጋፏን እንድታጠናክር ማገዛቸውን የሃማስ አመራሮች ይገልጻሉ።
ሃማስ በጥቅምት ወር 2023 በእስራኤል ላይ ድንገተኛ ጥቃት ከከፈተ ከቀናት በኋላም በኢራን ከሚደገፈው የሊባኖሱ ሄዝቦላህ መሪ ሀሰን ናስራላህ ጋር ሲመክሩ ታይተዋል።
እስራኤል በጋዛ ጦርነት ከጀመረች ወዲህ የቡድኑ ቃል አቀባይ ሆነው ለአልጀዚራ እና ሌሎች መገናኛ ብዙሃን አስተያየታቸውን ሲያጋሩ የቆዩት ግለሰቡ ከኳታርና ግብጽ አደራዳሪዎች ጋር በቀጥታ በመነጋገር በጋዛ የተኩስ አቁም እንዲደረስ ጉልህ ድርሻ ነበራቸው ተብሏል።
የሃማስን ወታደራዊ ክንፍ አል ቃሳም ብርጌድ በማቋቋሙ ሂደት ከፍ ያለ ድርሻ የነበራቸው ሳሌህ አል አኑሪ ከአመታት የስደት ህይወት በኋላ የቀደሙት የሃማስ መሪዎች እጣ ደርሷቸዋል።
የሊባኖሱ ሄዝቦላህና ኢራንም የሃማስ የፖለቲካ ቢሮ ምክትል ሃላፊውን ግድያ ለመበቀል በእስራኤል ላይ እርምጃ እንደሚወስዱ ዝተዋል።
የአል አኑሪ ግድያ በሊባኖስ፣ ሶሪያ፣ ኢራቅና የመን በቴህራን የሚደገፉት ሃይሎች በእስራኤል እና ሃማስ ጦርነት ተሳትፏቸውን እንደሚያጠናክረውና የጦርነቱን አድማስ እንደሚያሰፋው እየተነገረ ነው።