እስራኤል እና አውሮፓ በጋዛ የድህረ ጦርነት ጉዳዮች ላይ ሊወያዩ ነው
በዛሬው ዕለት የእስራኤል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አውሮፓ በጋዛ መልሶ ግንባታ ላይ በሚኖረው ሚና ከአህጉሩ ከፍተኛ ባለስልጣናት ጋር ይመክራሉ

ጦርነቱ ባስከተለው ጉዳት እና የንጹሀን ሞት በእስራኤል ላይ ትችት የሰነዘሩ የአውሮፓ ሀገራት እንደነበሩ ይታወሳል
እስራኤል እና አውሮፓ ጋዛን በተመለከቱ የድህረ ጦርነት ጉዳዮች ላይ በዛሬው ዕለት በብራሰልስ እንደሚመክሩ ተሰምቷል፡፡
የሀገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌድዮን ሳር በጋዛ እና ቀጠናዊ ጉዳዮች ላይ ከአውሮፓ ህብረት ከፍተኛ ባለስልጣናት እና ከአውሮፓ እስራኤል ህብረት ምክር ቤት አመራሮች ጋር እንደሚመክሩ ተነግሯል፡፡
ባለፈው ወር ተግባራዊ የሆነውን የጋዛ ተኩስ አቁም ስምምነትን ተከትሎ የአውሮፓ ህብረት በጋዛ መልሶ ግንባታ ላይ መሳተፍ እንደሚፈልግ ገልጿል፡፡
በዛሬው ዕለት የሚደረገው ጉባኤም በጋዛ ሰብአዊ ጉዳዮች ላይ እንዲሁም ቅርጹ እየተቀየረ በሚገኘው ቀጠና የአውሮፓ እና እስራኤል ግንኙነት ምን መምሰል እንደሚኖርበት ለመነጋገር መሆኑን በአውሮፓ የእስራኤል አምባሳደር ሃይም ሬጌቭ ተናግረዋል፡፡
ሮይተርስ አገኘሁት ባለው ረቂቅ ሰነድ ላይ ደግሞ የአውሮፓ ህብረት ለእስራኤል ደህንነት ድጋፍ ለማድረግ ያለውን ቁርጠኝነት እና የተፈናቀሉ የጋዛ ነዋሪዎች ወደ ቤታቸው በሰላም እና በክብር እንዲመለሱ መደረግ እንደሚኖርበት አፅንዖት ይሰጣል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
በዚህ ወር መጀመሪያ ላይ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የጋዛ ነዋሪዎችን በማፈናቀል አሜሪካ ጋዛን እንድትቆጣጠር ሀሳብ በማቅረብ የአረብ ሀገራትን እና ምዕራባውያንን አጋሮቻቸውን ያስቆጣ ንግግር አድርገው ነበር።
የጥቅምት ሰባቱን የሀማስ ጥቃት ተከትሎ እስራኤል በጋዛ ባወጀችው ጦርነት አውሮፓውን ሁለት አይነት ሀሳብን ሲያንጸባርቁ ቆይተዋል፡፡
የሀማስን ጥቃት ሁሉም ሀገራት አውግዘው የነበረ ሲሆን ጦርነቱ እየገፋ ሲሄድ አንዳንዶች ከእስራኤል ጎን ሲቆሙ ሌሎች ደግሞ ግጭቱ እያደረሰ የነበረው ውድመት እና የንጹሀን ሞትን በመቃወም ቴልአቪቭን ተችተዋል፡፡
በየካቲት 2024 የስፔን እና የአየርላንድ መሪዎች እስራኤል በ 2000 የአውሮፓ ህብረት እና የእስራኤል ማህበር ስምምነት መሠረት የሰብአዊ መብቶች ግዴታዎችን እየተወጣች እንደሆነ እንዲገመገም ለአውሮፓ ኮሚሽን ደብዳቤ ልከዋል።
ነገር ግን ከሰኞው ስብሰባ በፊት የህብረቱ 27 አባል ሀገራት ከእስራኤል ጋር የሚደረገውን የትብብር መስኮችን የሚያወድስ እና የተኩስ አቁምን ዘላቂነት እና አፈጻጸም ላይ ያሏቸውን ስጋቶች በማሳየት የጋራ አቋም አንጸባርቀዋል፡፡