አሜሪካ እና አውሮፓ አይናቸውን የጣሉበት የ15 ትሪሊዮን ዶላሩ የዩክሬን ማዕድናት
አሜሪካ በጦርነቱ ወቅት ለሰጠሁሽ ድጋፍ ማዕድንሽን ካልሰጠሸኝ ብላለች

በሩሲያ የተያዙት የዩክሬን ግዛቶች ከ350 ቢሊዮን ዶላር በላይ የሚያወጡ ማዕድናትን ይዘዋል ተብሏል
አሜሪካ እና አውሮፓ አይናቸውን የጣሉበት 15 ትሪሊዮን ዶላር የሚያወጣው የዩክሬን ማዕድናት
ከሶስት ዓመት በፊት ሩሲያ ለጥቂት ቀናት በሚል ልዩ ዘመቻ ጦሯን ወደ ዩክሬን መላኳን ተከትሎ የተጀመረው ጦርነት አሁንም እንደቀጠለ ይገኛል፡፡
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በምርጫ ወደ ስልጣን ከመጡ በኋል ጦርነቱ የሚቆምበት መላ እየተፈለገ ይገኛል፡፡
ይህን ተከትሎ ለዩክሬን ዋነኛ የጦር መሳሪያ እና ገንዘብ ድጋፍ አድራጊ የነበረችው አሜሪካ ድጋፏን አቁማለች፡፡
ይህን ተከትሎም ፕሬዝዳንት ትራምፕ አሜሪካ ለዩክሬን ለሰጠችው በመቶ ቢሊዮን ዶላሮች መልሽልን አልያም ማዕድንሽን ስጪኝ የሚል ቀጥተኛ ጥያቄ አቅርበዋል፡፡
የዩክሬን ፕሬዝዳንት ቮሎዶሚር ዘለንስኪ የፕሬዝዳንት ትራምፕን ጥያቄ ውድቅ አድርገናል ቢሉም የማዕድን ስምምነት በጋራ በመዘጋጀት ላይ እንደሆነ ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
ዩክሬን አሁን ላይ እና ወደፊት ተፈላጊ የሚሆኑ ውድ ማዕድናት መገኛ ናት የተባለ ሲሆን በተለይም ብረት፣ ዩራኒየም፣የከሰል ድንጋይ፣ሊቲየም እና ሌሎች ተፈላጊ ማዕድናት አሏት፡፡
እንደ ፎርብስ ዘገባ ከሆነ ዩክሬን 15 ትርሊዮን ዶላር የሚያወጣ ማዕድናት ያሏት ሲሆን ከነዚህ ውስጥ 350 ቢሊዮን ዶላር ዋጋ ያላቸው ብረት እና ሊቲየም ማዕድናት የሚገኙት ሩሲያ በተቆጣጠሯቸው ግዛቶች ውስጥ ነው፡፡
የጦርነቱ ዋነኛ ደጋፊ የነበረችው አሜሪካ እስካሁን ላወጣሁት ወጪ ማዕድኖችሽን አሳልፊና ስጪኝ ስትል የአውሮፓ ህብረት ሀገራት ደግሞ ለዩክሬን ተጨማሪ የጦር መሳሪያ ድጋፍ ስለሚያደርጉበት ሁኔታ በመምከር ላይ ናቸው፡፡
ሊቲየም ማዕድን በብዛት ከሚገኝባቸው የዓለም ሀገራት መካከል ዩክሬን አንዷ ስትሆን ይህ ማዕድን ኤሌክትሮኒክስ ምርቶችን ጨምሮ ለአቪዬሽን ኢንዱትሪ ጠቃሚ የሆኑ ምርቶችን ለማምረት ተፈላጊ ነው፡፡
ጦርነቱን እንድታቆም ጫና የበዛባት ዩክሬን ከአሜሪካ ጋር የማዕድን ስምምነት በያዝነው ሳምንት ልትፈራረም እንደምትችል ይጠበቃል፡፡