ፕሬዝዳንት ሼክ መሃመድ ቢን ዛይድ ይፋዊ የስራ ጉብኝት ለማድረግ ጣሊያን ገቡ
ሼክ መሃመድ ቢን ዛይድን የያዘው አውሮፕላንን የጣሊያን የጦር ጄቶች አየር ላይ አቀባበል አድርገው እጀበዋል

ፕሬዝዳንት ሼክ መሀመድ ቢን ዛይድ በጣሊያን ፕሬዝዳንት ሰርጂዮ ማታሬላ በተዘጋጀ የእራት ግብዣ ላይ ተገኝተዋል
የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ፕሬዝዳንት ሼክ መሀመድ ቢን ዛይድ አል ናህያን በጣሊያን ይፋዊ የስራ ጉብኝት ለማድረግ ሮም ገብዋል።
ፕሬዝዳንት ሼክ መሀመድ ቢን ዛይድን የያዘው አውሮፕላን የጣሊያን አየር ክልል ውስጥ ሲገባም የሀገሪቱ የጦር ጄቶች አየር ላይ አቀባበል አድርገው እንዳጀቧው የኢምሬትስ የዜና ኤጀንሲ (ዋም) ዘግቧል።
ፕሬዝዳንት ሼክ መሀመድ ቢን ዛይድ ትናንት ምሽት ላይ ሮም የደረሱ ሲሆን ይፈዊ የስራ ጉብኝታቸውን ዛሬ ይጀምራሉ።
በጉብኝቱም ፕሬዝዳንት ሼክ መሀመድ ቢን ዛይድ አል ናህያን ከጣሊያን ፕሬዝዳንት ሰርጂዮ ማታሬላ እና ከጠቅላይ ሚኒስትር ጆርጂያ ሜሎኒ ጋር በተለያዩ የትብብር ዘርፎች ዙሪያ እንደሚወያዩ ይጠበቃል።
በተለይም በአረብ ኤምሬትስ እና በጣሊያን መካከል ባለው ስትራቴጂካዊ አጋርነት ማዕቀፍ መሰረት በኢኮኖሚ፣ በኢንቨስትመንት፣ በታዳሽ ሃይል፣ የላቀ ቴክኖሎጂ እና አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ መስኮች ላይ እንደሚወያዩ ይጠበቃል።
ፕሬዝዳንት ሼክ መሀመድ ቢን ዛይድ ከጉብኝቱ ቀደም ብሎ ትናንት ምሽት በጣሊያን ፕሬዝዳንት ሰርጂዮ ማታሬላ በተዘጋጀ የእራት ግብዣ ላይ ተገኝተዋል።
ፕሬዝዳንት ሰርጂዮ ማታሬላ የአረብ ኤሚሬትስ ፕሬዝዳንት ሼክ መሀመድ ቢን ዛይድ አል ናህያንን በጣሊያን ይፋዊ ጉብኝት ለማድረግ ሮም በመግታቸው የተሰማቸውን ደስታ ገልጸው፤ በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን ግንኙነት እና ትብብር ለማሳደግ ፍላጎት እንዳላቸው አስታውቀዋል።
ፕሬዝዳንት ሼክ መሀመድ ቢን ዛይድ አል ናህያን በበኩላው ፕሬዚዳንት ሰርጂዮ ማታሬላ ላደረጉላቸው ደማቅ አቀባበል እና መልካም ንግግራቸው አመስግነው፤ በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን ግንኙነት የበለጠ ለማሳደግ ፍላጎት እንዳላቸው ገልጸዋል።
ሼክ መሀመድ ቢን ዛይድ “በተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች እና በጣሊያን መካከል ያለው ስትራቴጂካዊ ግንኙነት ወደ ተጨማሪ ልማት እና እድገት እየገሰገሰ ነው” ብለዋል።
“ጉብኝታችን በአረብ ኤምሬትስ እና በጣሊያን መካከል ያለው ልዩ ስትራቴጂካዊ አጋርነት ትልቅ ለውጥ ለማምጣት በጋራ ለመስራት ያለንን ፍላጎት ያሳያል” ሲሉም ተናግረዋል።
በእራት ግብዣው ላይ የአረብ ኤሚሬትስ ፕሬዝዳንት ሼክ መሀመድ ቢን ዛይድ አል ናህያን እና የጣሊያን ፕሬዝዳንት ሰርጂዮ አንዳቸው ለአንዳቸው ሜዳሊያ ሸልመዋል።
በዚህም ወቅት ፕሬዝዳንት ሼክ መሀመድ ቢን ዛይድ ለጣሊያኑ ፕሬዝዳት ሰርጂዮ ማታሬላ የተባሩት አረብ ኤምሬትስ ከፍተኛ የክብር ሜዳሊያ የሆነውን “የዛይድ ሜዳሊያ” አበርክተዋል።
ፕሬዝዳንት ሰርጂዮ ማታሬላም ለፕሬዝዳት ሼክ መሃመድ ቢን ዛይድ ጣሊያን ለመሪዎች፣ ለንጉሶች እና ፕሬዝዳንቶች የምትሰጠውን ከፍተኛው ሜዳሊያ አብርክተዋል።
የሁለቱን ሀገራት ታሪክ እና ቅርስ የሚያሳዩ በርካታ ስጦታዎችንም ተለዋውጠዋል።