እርምጃው የሰብዓዊ እርዳታ እንቅስቃሴዎች ላይ ተጽዕኖ እንደማይኖረው ህብረቱ ገልጿል
የአውሮፓ ህብረት በሀምሌ ወር የኒጀርን ፕሬዝዳንት ከስልጣን ባወረደው የወታደራዊ አስተዳደር አባላት ላይ ማዕቀብ ለመጣል ማዕቀፍ ማጽደቁን አስታውቋል።
እርምጃው ለኒጀር አለመረጋጋት፣ ዲሞክራሲ እና የህግ የበላይነት እጦት እንዲሁም ለአካባቢው ሰላም እና ደህንነት ጠንቅ የሆኑትን ለመቅጣት ያለመ መሆኑን ህብረቱ በመግለጫው አመልክቷል።
የአውሮፓ ህብረት የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ኃላፊ ጆሴፍ ቦሬል አዲሱ ማዕቀፍ ህብረቱ የኒጀርን ሰላም፣ መረጋጋትና ደህንነት አደጋ ላይ የሚጥሉ ድርጊቶችን በሚፈጽሙ ግለሰቦችና አካላት ላይ ማዕቀብ መጣል ይችላል ብለዋል።
"የእገዳ እርምጃው የንብረት ማገድ እና ለግለሰቦች እና ለድርጅቶች ገንዘቦችን ማገድን እንዲሁም ለግለሰቦች የጉዞ እገዳን ያካትታል" ብለዋል።
የቀድሞ የፕሬዝዳንታዊ ጠባቂ አዛዥ ጄነራል አብዱራሃማኔ ቺያኒ ፕሬዝዳንት መሀመድ ባዙምን ባለፈው ሀምሌ ወር ከስልጣን አስወግደዋል።
ከጅምሩ ወታደራዊውን ጣልቃ ገብነት ያወገዘው የአውሮፓ ህብረት፤ አዲሱ ማዕቀፍ የምዕራብ አፍሪካ ሀገራት የኢኮኖሚ ማህበረሰብ (ኢኮዋስ) ሀገሪቱን በፍጥነት ወደ ህገ-መንግስታዊ ስርዓት ለመመለስ የሚያደርገውን ጥረት ይደግፋል ብሎ እምነት ይዟል።
ማዕቀፉ "ግልጽ መልእክት ይልካል። ወታደራዊ መፈንቅለ መንግስት ዋጋ ያስከፍላል የሚል ነው" ማለቱን አናዶሉ ዘግቧል።
ይሁን እንጂ አዲሶቹ እርምጃዎች የሰብዓዊ እርዳታ እንቅስቃሴዎች ላይ ተጽዕኖ እንደማይኖራቸው ህብረቱ ገልጿል።