ፈረንሳይ በማሊ 1 ሺህ 500 ወታደሮችን አስፍራለች
ፈረንሳይ በኒጀር ያሏትን ወታደሮች እንደማታስወጣ ገለጸች።
ምዕራብ አፍሪካዊቷ ኒጀር ከአንድ ወር በፊት በተፈጸመ መፈንቅለ መንግሥት የቀድሞው ፕሬዝዳንት ጥበቃ ክፍል አዛዥ ጀነራል ቲያኒ መሪነት ስልጣን ተቆጣጥረዋል።
ፈረንሳይ በሀይል ከስልጣን ከተወገዱት የቀድሞ ፕሬዝዳንት ባዙም ጋር ጥብቅ ግንኙነትን በመመስረት የኒጀርን ሀብት እየመዘበረች ነው የሚል ክስ ቀርቦባታል።
ይህን ተከትሎም ፈረንሳይ አሁንም የቀድሞውን ፕሬዝዳንት ወደ ስልጣን ለመመለስ በመንቀሳቀስ ላይ እንደሆነችም ተገልጿል።
ስልጣን በሀይል የተቆጣጠረው የኒጀር ወታደራዊ ቡድንም የፈረንሳይ አምባሳደር ኒያሚን ለቀው እንዲወጡ ያስተላለፈውን ትዕዛዝ ሳይቀበሉ ቀርተዋል ተብላል።
በተሰጣቸው ጊዜ ኒጀርን ለቀው ያልወጡት የፈረንሳይ አምባሳደር የዲፕሎማሲ ከለላ መብታቸው መነሳቱ ተገልጻል።
ፈረንሳይ በበኩሏ ስልጣን በሀይል የተቆጣጠረው ወታደራዊ ቡድን በኒያሚ ያለውን አምባሳደር የማባረር ስልጣን እንደሌለው ወታደሮቿም በዛው እንደሚቆዩ አስታውቃለች።
የፈረንሳይ ውጪ ጉዳይ ሚንስትር ካትሪን ኮሎና ለለሞንዴ ጋዜጣ እንዳሉት "በኒጀር የፈረንሳይ አምባሳደር ሲልቪያን ኢቴ በኒያሚ ህጋዊ ስልጣን ካለው የፕሬዝዳንት መሀመድ ባዙም ጋር መስራታቸውን ይቀጥላሉ፣ ወታደሮቻችንንም ከኒጀር አናስወጣም " ብለዋል።
ኒጀራዊያን ግን በኒያሚ ባለው የፈረንሳይ ኢምባሲ ፊት ለፊት በመቅረብ ከሀገራቸው ለቀው እንዲወጡ በተደጋጋሚ በሰላማዊ ሰልፍ በመጠየቅ ላይ ናቸው።
በተያያዘ የአፍሪካ ዜና ባሳለፍነው ሳምንት ሌላ መፈንቅለ በተፈጸመባት ጋቦን ጊዜያዊ ፕሬዝዳንት ተደርገው የተመረጡት ጀነራል ኦሊጊ ንጉማ ቃለ መሀላ እንደሚፈጽሙ ይጠበቃል።
ላለፉት 14 ዓመታት የጋቦን ፕሬዝዳንት የነበሩት አሊ ቦንጎ ከፕሬዝዳንትነታቸው በሀይል ተነስተዋል ተብሏል።
እንዲሁም ለሁለተኛ ጊዜ ምርጫ ማሸነፋቸውን ያወጁት የዚምባብዌ ፕሬዝዳንት ኤመርሰን ምናጋግዋ በዓለ ሲመት ያደርጋሉም ተብሏል።