የሶማሊያ ጎረቤት ሀገራት ወታደሮችን ለማሰልጠን ተስማሙ
ኢትዮጵያ ፣ ግብጽ፣ ኡጋንዳ እና ኤርትራ የሶማሊያን ጦር ለማሰልጠን ከተስማሙ ሀገራት መካከል ዋነኞቹ ናቸው
ሶማሊያ በተያዘው ዓመት ብቻ 15 ሺህ ወታደሮችን የማሰልጠን እቅድ እንዳላት ተገልጿል
የሶማሊያ ጎረቤት ሀገራት ወታደሮችን ለማሰልጠን ተስማሙ።
ከአልሻባብ ጋር እልህ አስጨራሽ ጦርነት ላይ የምትገኘው ሶማሊያ ጎረቤት ሀገራት ወታደሮች እንዲያሰለጥኑላት ጠይቃለች ተብሏል።
የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚንስትር አብይ አህመድ፣ የኬንያው ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ እና የጅቡቲው ፕሬዝዳንት እስማኤል ኦማር ጊሌ በሶማሊያ መዲና መቋዲሾ ተገናኝተው በአልሻባብ ጉዳይ መወያየታቸው ይታወሳል።
እንደ ቪኦኤ ዘገባ ከሆነ በተያዘው የፈረንጆቹ 2023 ዓመት ብቻ ሶማሊያ 15 ሺህ ወታደሮቿን ወደ ጎረቤት ሀገራት በመላክ ማሰልጠን ትፈልጋለች።
በዚህ መሰረትም ኤርትራ እና ኡጋንዳ እያንዳንዳቸው ሶስት ሶስት ሺህ ወታደሮችን ለማሰልጠን ተስማምተዋል።
የሶማሊያ ወታደሮች ወደ አስመራ እና ካምፓላ ተልከዋል የተባለ ሲሆን ስድስት ሺህ የሶማሊያ ሰልጣኝ ወታደሮችም ወደ ኢትዮጵያ እና ግብጽ በቅርቡ ይላካሉ ተብሏል።
ሶማሊያ በፈረንጆቹ እስከ 2024 ድረስ 24 ሺህ ወታደሮችን የማሰልጠን እቅድ እንዳላት ተገልጿል።
አፍሪካ ህብረት ከምስራቅ አፍሪካ ሀገራት የተውጣጣ ሰላም አስከባሪ ጦር ወደ ሶማሊያ የላከ ሲሆን ቀስበቀስ ይህ ጦር እንደሚወጣ ይጠበቃል።
በኤርትራ የሰለጠኑ አምስት ሺህ የሶማሊያ ወታደሮች በቅርቡ ወደ ሞቃዲሾ ተመልሰው ከአልሻባብ ጋር የተጀመረውን ጦርነት እንደተቀላቀሉ ተገልጿል።
ሶማሊያ እስከ ቀጣዩ ክረምት ድረስ አልሻባብ የተሰኘውን የሽብር ቡድን ሙሉ ለሙሉ የመደምሰስ እቅድ እንዳላት ከዚህ በፊት ማሳወቋ ይታወሳል።