የአውሮፓ ህብረት ተለዋጭ ፕሬዝዳንት ስዊድን "ለዩክሬን ጦር ኃይሎች በምናደርገው ድጋፍ ጸንተናል" ብላለች
የአውሮፓ ህብረት የውጭ ጉዳይ ሚንስትሮች ለዩክሬን ተጨማሪ 542 ሚሊዮን ዶላር ለመመደብ ተስማምተዋል።
ስምምነቱ የተደረሰው የአውሮፓ ህብረት 27 የውጭ ጉዳይ ሚንስትሮች በብራስልስ ተገናኝተው ባለፈው ሳምንት ምዕራባውያን ሀገራት ለዩክሬን ተዋጊ ታንኮችን ለመላክ መስማማት አለመቻላቸውን ተከትሎ ነው።
የውጭ ጉዳይ ሚንስትሮቹ የአውሮፓ ህብረት ለዩክሬን ወታደራዊ ማሰልጠኛ ተልዕኮ በተጨማሪ 45 ሚሊዮን ዩሮ "ገዳይ ላልሆኑ መሳሪያዎች" ማፅደቃቸውን የስዊድን እና የቼክ ባለስልጣናት አስታውቀዋል።
የአውሮፓ ህብረትን ተለዋጭ የፕሬዝዳንትነት ቦታ የያዘችው ስዊድን "ለዩክሬን ጦር ኃይሎች በምናደርገው ድጋፍ ጸንተናል" ስትል መናገሯን ሮይተርስ ዘግቧል።
በርሊን ለኪየቭ ጀርመን ሰራሽ የሆኑትን "የሊዮፓርድ ታንኮችን" እንድታቀርብ ተጨማሪ ጫና ገጥሟታል ነው የተባለው።በመላው አውሮፓ በጦር ኃይሎች አለ የተባለው የጀርመን ታንክ ለዩክሬን ተስማሚ ሆኖ ታይቷል
ሆኖም በርሊን ታንኮቹ እንዲሸጡ መፍቀድ ያለባት ሲሆን፤ እስካሁን ግን አልተስማማችም ተብሏል። ጀርመን ሩሲያ ልትወስድ ትችላለች ባለችው እርምጃ ስጋት እንደገባት እየተነገረ ነው።
ፖላንድ ሰኞ እለት የሊዮፓርድ ታንኮችን ወደ ዩክሬን ለመላክ ጀርመንን ፈቃድ እንደምትጠይቅ ተናግራለች።