የአውሮፓ ህብረት በአውሮፕላን ነዳጅ ላይ ግብር ለመጣል ማቀዱ ተነገረ
ህብረቱ በኮፕ28 የሚያቀርበው የውሳኔ ሃሳብ በቻይና እና በባህረሰላጤው ሀገራት ድጋፍ ማግኘቱንም አስታውቋል
የአውሮፕላን ነዳጅ (ኬሮሲን) ከሌሎች የነዳጅ አይነቶች በተለየ ግብር አይጣልበትም
የአውሮፓ ህብረት በዱባይ እየተካሄደ በሚገኘው 28ኛው የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ በአውሮፕላን ነዳጅ ላይ ግብር እንዲጣል የሚጠይቅ የውሳኔ ሃሳብ እንደሚያቀርብ ተገለጸ።
ፋይናንሽያል ታይምስ ይዞት የወጣው ዘገባ እንደሚያመላክተው ህብረቱ በአውሮፕላን ነዳጅ ላይ አለማቀፍ ግብር እንዲጣል ፍላጎት አለው።
የህብረቱ የአየር ንብረት ለውጥ ኮሚሽነር ዎፕኪ ሆኪስትራ እንደገለጹት፥ በአውሮፕላን ነዳጅ ላይ ግብር እንዲጣል የቀረበውን ሃሳብ ቻይና፣ ብራዚል፣ ዛምቢያ እና የተለያዩ የባህረ ሰላጤው ሀገራት ደግፈውታል።
የአውሮፕላን ነዳጅ (ኬሮሲን) እንደሌሎች የነዳጅ አይነቶች በመላው አለም ግብር አይጣልበትም።
አውሮፕላኖች በእያንዳንዱ ጉዟቸው በከባቢ አየር ላይ ለሚለቁት በካይ ጋዝ የሚከፍሉት ገንዘብ የአየር ብክለትን ለመቀነስ ለሚውሉ ስራዎች ያግዛል ሲሉም ነው ዎፕኪ ሆኪስትራ በብራሰልስ ለጋዜጠኞች የተናገሩት።
ግብሩ የሚጣለው በአውሮፓ፣ ሰሜን አሜሪካ እና ሌሎች የበለጸጉና ዜጎቻቸው የአየር ትራንስፖርትን በስፋት በሚጠቀሙ ሀገራት መሆኑንም አብራርተዋል።
ፈረንሳይ በባህር ላይ በሚቀዝፉ መርከቦች ላይም መሰል ግብር በመጣል የአየር ንብረት ቀውስን ለመቀነስ ማቀዷ ተመላክቷል።
የታዳሽ ሃይል ሽግግርን እንደሚያፋጥን የታመነበት የውሳኔ ሃሳብ ዝርዝር ጉዳዮች በኮፕ28 ጉባኤ እንደሚገለጽ ነው የአውሮፓ ህብረት ያስታወቀው።
የተለያዩ ሀገራት መንግስታት ከባቢ አየርን በሚበክሉ ኢንዱስትሪዎች ላይ የቅጣት ክፍያ ለማስከፈል መዘጋጀታቸውንም የፋይናንሽያል ታይምስ ዘገባ አመላክቷል።