ከባዮማስ የሚሰራው የአውሮፕላን ነዳጅ
“ዘላቂ የአቪየሽን ነዳጅ” (ኤስኤኤፍ) በአውሮፕላን በረራ ወቅት እየደረሰ ያለውን ብክለት በ80 በመቶ ይቀንሳል ተብሏል
ውድ መሆኑና ከፍተኛ መዋዕለ ንዋይን መጠየቁ ግን በፍጥነት ጥቅም ላይ የመዋሉን ነገር አጠራጣሪ አድርጎታል
አንድ የአውሮፕላን በረራ 56 በተለያዩ ሀገራት የሚኖሩ ሰዎች በአመት ውስጥ ከባቢ አየርን የሚበክሉትን ያህል የካርበን ልቀት ያስከትላል።
በአውሮፕላን በረራ ወቅት የሚደርሰው የከባቢ አየር ብክለት በየአመቱ እየጨመረ መምጣቱን የአለማቀፉ የአቪየሽን ትራንስፖርት ድርጅት (አይታ) መረጃ ያሳያል።
ድርጅቱ በመላው አለም በ2050 ከካርበን ልቀት የጸዳ በረራን ለማካሄድ የያዘው እቅድም የመሳካቱን ነገር ከባድ የሚያደርጉት ነገሮች በርካታ ናቸው።
ዋነኛው የብክለት ምንጭም አውሮፕላኖች የሚጠቀሙት ነዳጅ ነው።
ይህን የነዳጅ አይነት የሚተካውና እስከ 80 ከመቶ የካርበን ብክለት የሚቀንስ የነዳጅ አይነት ከተዋወቀ አመታት ቢቆጠሩም እስካሁን ጥቅም ላይ የዋለው ከ0 ነጥብ 1 በመቶ አልበለጠም።
የአውሮፕላን ነዳጅን የሚተካው “ኤስኤኤፍ” ምንድን ነው?
“ዘላቂ የአቪየሽን ነዳጅ” ወይም “ኤስኤኤፍ” ከባዮማስ (አልጌ፣ የእንሰሳት ቅሪት፣ ከምግብ እና ከቆሻሻ) የሚዘጋጅና ከብክለት የጸዳ የቀጣዩ የአቪየሽን ኢንዱስትሪ ተስፋ ነው።
በካዩን የአውሮፕላን ነዳጅ (ፔትሮሊየም) የሚተካው “ኤስኤኤፍ” ከእንሰሳት እና እጽዋት የሚዘጋጅ እንደመሆኑ የካርበን ብክለትን አያስከትልም ቢባልም አዲስ እንደመሆኑና ለማምረት ወድ ዋጋ መጠየቁ በስፋት ጥቅም ላይ የመዋሉን ነገር አስቸጋሪ ያደርገዋል።
አሁን ላይ ጥቅም ላይ እየዋለ ካለው የአውሮፕላን ነዳጅ አንጻር ቀላልና የሚሰጠው ሃይል (በ1 ሊትር የሚያስጉዘው) ዝቅተኛ መሆኑም ሌላኛው ፈተና መሆኑን የአውሮፓ ህብረት ጥናት ያሳያል።
የአውሮፓ የአቪየሽን ኢንዱስትሪን ከካርበን ብክለት የጸዳ ለማድረግና አዲሱን የሃይል አማራጭ ለማምረት 440 ቢሊየን ዶላር የሚያወጣ ኢንቨስትመንት መጠየቁም ነው የተነገረው።
አዲሱን ከብክለት የጸዳ የአውሮፕላን ነዳጅ ለማምረት በርካታ መሰናክሎች እንዳሉ ቢነሳም አንዳንድ አየርመንገዶች ከተለመደው ነዳጅ ጋር በመቀላቀል እየሞከሩት ነው ተብሏል።
በአለማቀፍ ደረጃ በ2050 የተያዘውን ብክለትን ዜሮ የማድረስ እቅድ ለማሳካት ይህን የነዳጅ አማራጭ መጠቀሙ ፋይዳው ትልቅ መሆኑ አጠራጣሪ ባይሆንም ሀገራት ብዙም ኢንቨስት እያደረጉበት አይደለም።