ሩሲያ ኔቶ ከምስራቃዊ አውሮፓ ሀገራት ለቆ እንዲወጣ አስጠነቀቀች
ኔቶ በቀድሞው የሶቪዬት ህብረት ስር ከነበሩ ሀገራት ጦሩን እንዲያስወጣ ሩሲያ አሳስባለች
ሩሲያ ከኔቶ ጋር ለመደራደር ዝግጁ መሆኗን ገልጻለች
የሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃል ኪዳን ኔቶ ከምስራቃዊ አውሮፓ ሀገራት ለቆ እንዲወጣ ሩሲያ አስጠነቀቀች፡፡
የሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃል ኪዳን ወይም ኔቶ ዩክሬንን በአባልነት ለማስገባት ከጫፍ መድረሱን ተከትሎ ኔቶ እና ሩሲያ ተፋጠዋል፡፡
ዩክሬን የኔቶ አባል ከሆነች የደህንነት ስጋት አለኝ በሚል በጉዳየ የተበሳጨችው ሩሲያ ሉዓላዊነቴን ለማስከበር ስል እርምጃ ለመውሰድ እገደዳለሁ በሚል ማስጠንቀቋ ይታወሳል፡፡
የሩሲያን ማስጠንቀቂያ ተከትሎም አሜሪካ እና ሌሎች ምዕራባዊያን ሀገራት ሩሲያ ዩክሬንን ልትወር ትችላለች በማለት ላይ ሲሆኑ በምስራቃዊ አውሮፓ እና አካባቢው ውጥረት ነግሷል፡፡
ሩሲያም በአካባው የተፈጠረው ውጥረት እንዲረግብ ከተፈለገ ኔቶ በምስራቃዊ አውሮፓ በተለይም በቀድሞ የሶቪየት ህብረት አባል ሀገራት ስር በነበሩ ሀገራት ውስጥ ያሰማራውን ጦር ለቆ እንዲወጣ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴሯ በኩል አስጠንቅቃለች፡፡
ሩሲያ ከዚህ በተጨማሪም ከኔቶ አባል ሀገራት ጋር በጄኔቭ በየትኛውም ቦታ ለመደራደር ዝግጁ መሆኗን የሀገሪቱ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ሰርጊ ሪያብኮቭ ገልጸዋል፡፡
ምዕራባዊያን ሀገራት ከሩሲያ ጋር በተያያዘ ያለባቸውን ችግር ለመፍታት እንደ አዲስ ሊወያዩ ያገባል ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው አሜሪካንን ጨምሮ ኔቶ እና ምዕራብ አገራት የሩሲያን ደህንነት አደጋ ላይ ከመጣል እንዲቆጠቡ አሳሰሰበዋል፡፡
ሩሲያ ከዚህ በተጨማሪም የኔቶ ጦር ዩክሬንን በአባልነት እንዳይቀበል፣ተጨማሪ ጦር ወደ ምስራቃዊ አውሮፓ እና ማዕከላዊ እስያ ሀገራት እንዳያሰፍር፣ወታደራዊ እንቅስቃሴ እንዳያደርግ፣ ሚሳኤሎችን እንዳይተክሉ፣ ከአንድ ብርጌድ በላይ ወታደራዊ ሀይል የጦር ልምምድ እንዳይደርግ፣ ውጥረቶችን በሀይል ለመፍታት አለመሞከር እና ሌሎችንም በቅድመ ሁኔታነት አስቀምጣለች፡፡
ሩሲያ እነዚህን የቅድመ መደራደሪያ ሁኔታዎችን ለአሜሪካ እና ለሌሎቸር አባል አገራት ማድረሷን የገለጸች ሲሆን ኔቶ እና አባል ሀገራቱ እስካሁን የሰጡት ምላሽ እንደሌለ ተገልጿል፡፡
የሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃል ኪዳን ወይም ኔቶ ከ70 ዓመት በፊት በ13 ሀገራት የተመሰረተ ሲሆን አሁን ላይ 30 ዓባላት አሉት፡፡
አሜሪካ፣ጀርመን፣ቱርክ እና ፈረንሳይ ደግሞ ከኔቶ አባላ አገራ መካከል በርካታ ጦር ያዋጡ ሀገራት ሲሆኑ አሜሪካ ከ1 ሚሊዮን በላይ ሰራዊት በማዋጣት ቀዳሚዋ ናት፡፡አይስላንድ፣ሉግዘንበርግ እና ሜንቴኔግሮ ደግሞ በኔቶ ውስጥ ዝቅተኛ የጦር ሰራዊት ያዋጡ አባል ሀገራት ናቸው፡፡