ፖፕ ፍራሲስ በአውሮፓ ያለውን የስደተኞች አያያዝ አወገዙ
የአውሮፓ ሀገራት ስደተኞችን እያስተናገዱበት ያለው መንገድ“የስልጣኔ ውድቀት ነው” ብለዋል ፖፕ ፍራንሲስ
ፖፕ የሰደተኞች ጉዳይ መሰረታዊ መፍትሄ የሚሻ እንጂ “ለፖለቲካ ፍጆታ ሊውል የማይገባው ጉዳይ ነው” መሆኑን ገልጸዋል
የዓለም ካቶሊክ ቤተ-ክርስትያን ሊቃነ ጳጳስ ፍራንሲስ ሀገራት ስደተኞችን እየያዙበት ያለውን መንገድ አወገዙ፡፡
የግሪኳ የሌስቦስ ደሴት ተገኝተው ንግግር ያደረጉት ፖፕ ፍራንሲስ የአውሮፓ ሀገራት ስደተኞችን እያስተናገዱበት ያለው መንገድና አያያዝ “የስልጣኔ ውድቀት ነው” ሲሉ አውግዘውታል።
ፖፕ ፍራንሲስ እንደፈረንጆቹ በ2016 የስደተኞች ወደ ተለያዩ ሀገራት መዝለቅያ ሆና ወደ ምታገለግለው ሌስቦስ ደሴት በማቅናት ጎብኝተው የነበረ ሲሆን፤ አሁን ያለው የስደተኞች ቁጥር መጨመር ሁኔታና አያያዝ ተመሳሳይ መሆኑ እንዳሳዘናቸውም ገልጿል፡፡
ባለፈው ወር በትንሽ ጀልባ ከፈረንሳይ ወደ ብሪታንያ ሲሻገሩ የነበሩ 27 ስደተኞች በደሴቱ ላይ ሰምጠው ህይወታቸው እንዳለፈ የሚታወስ ነው፡፡
አሁን ላይ በደሴቱ ካናል የሚያልፉ ስደተኞች ቁጥር በእጅጉ እየጨመረ በመምጣቱ፤ እስካሁን ድረስ 26 ሺ ስደተኞች ወደ ታላቋ ብሪታንያ እንደገቡ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ ይህ ቁጥር ካለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር ከእጥፍ በላይ ጨምሯልም ነው የተባለው፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ ሌሎች በርካታ ስደተኞች ከቤላሩስ ወደ ፖላንድ ለማቋረጥ በሚሞክሩበት ወቅት በከፍተኛ ብርድ ምክንያት ህይወታቸው እንዳለፈም ይነገራል፡፡
ጳጳሱ ባለፈው በእሳት ምክንያት በወደመውና 2ሺ የጥገኝነት ጠያቂዎች የሚገኙበት ግዜያዊ የሞሪያ መጠለያ ጣቢያ ላይ ተገኝተው እንደተነገሩት ከሆነ “አውሮፓውያን ጉዳዩን እንደማይመከታቸው በቸልታ ማየታቸው የሚያሳዝን ነው” ብሏል፡፡
ፖፕ ፍራሲስ አክለው “የራስህን ጥቅም ላይ ብቻ ማተኮር የማይጠቅም ነው፤ የሚያስከትለው ነገር እንዳለም ታሪክ አስተምሮናል” ሲሉም ነው የተናገሩት።
ዓለም ለአየር ንብረት ለውጥ የሚሰጠውን ትኩረት ያክል ለስደተኞች እየሰጠ አይደለም ሲሉም ፖፕ ፍራንሲስ በንጽጽር አስረድቷል፡፡
የሰደተኞች ጉዳይ መሰረታዊ መፍትሄ የሚሻ እንጂ ለፖለቲካ ፍጆታ ሊውል የማይገባው ጉዳይ ነውም ብሏል ፍራንሲስ፡፡ የፖፕ ፍራንሲስ ንግግር የአውሮፓ ሀገራት ኃላፊነታቸውን እየተወጡ እንዳልሆነ ሸንቆጥ የሚያደርግ ተብሎለታል፡፡
ከጳጳሱ ጋር የተገኙት የግሪኳ ፕሬዝዳንት ካትሪና ሳኬለሮፑሉ፤ የስደተኞች ጉዳይ የግሪክ ብቻ ሳይሆን ሁሉንም ሀገራት የሚመለከት ነው ሲሉ ተደምጧል፡፡
በዚህ ዓመት ብቻ ከ8ሺ በላይ ሰዎች በየብስና በባህር ወደ ግሪክ የዘለቁ ሲሆን፤ ካለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር በ15 ሺ ስደተኞች ያነሰ ነው ተብሏል፡፡
ግሪክ ጥገኝነት የሚጠይቁ በርካታ ስደተኞች ለማቆየት የሚያስችሉ የተለያዩ መጠለያ ጣብያዎች በመገንባት ላይ እንደሆነችም ነው የተገለጸው፡፡ግሪክ ስደተኞች እንዳይገቡባት እየከለከለች ናት በሚል የሚቀርብባትን ክስም ውድቅ አድርጋለች፡፡