ሩሲያ አቋርጣው ወደነበረው የጥቁር ባህር ስንዴ ማጓጓዝ ስምምነት ተመለሰች
የዩክሬንን ማረጋጋጫ ተከትሎ ሩሲያ ዘግታው የነበረውን የጥቁር ባህር ንግድ መስመር ዳግም ከፍታለች
ዩክሬን በጥቁር ባህር ኮሪደር ላይ ዳግም ጥቃት እንደማታደርስ የጽሁፍ ማረጋገጫ ሰጥታለች ተብሏል
ሩሲያ አቋርጣው ወደነበረው የጥቁር ባህር ስንዴ ማጓጓዝ ስምምነት ተመለሰች፡፡
በተመድ እና ቱርክ አግባቢነት መሰረት የዩክሬን ስንዴ በሩሲያው ጥቁር ባህር አድርጎ የምግብ እጥረት ወዳለባቸው አካባቢዎች እንዲጓጓዝ ከሁለት ወር በፊት ሩሲያ እና ዩክሬን ስምምነት ላይ ደርሰው ነበር፡፡
በዚህ ስምምነት መሰረት 9 ነጥብ 3 ሚሊዮን ቶን ስንዴ ከዩክሬን ተነስቶ በጥቁር ባህር አድርጎ ለዓለም ገበያ መቅረቡን ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
ይሁንና ሩሲያ ባሳለፍነው ቅዳሜ ከዩክሬን በተሰነዘረ የሰው አልባ አውሮፕላን ጥቃት ስንዴ ጭነው ሲጓጓዙ የነበሩ መርከቦች ተጎድተዋል በሚል ከስምመነቱ መውጣቷን አስታውቃ ነበር፡፡
ዩክሬን በሩሲያ የቀረበውን ክስ በወቅቱ ውድቅ ያደረገች ቢሆንም የተባበሩት መንግስታት ድርጅት፣ አውሮፓ ህብረት እና አሜሪካ ሩሲያ ወደ ስምምነቱ እንደትመለስ ሲወተውቱ ቆይተዋል፡፡
ሩሲያ በበኩሏ የዩክሬን ስንዴ በጥቁር ባህር አድርጎ አይጓዝም ዩክሬን መልሳ ጥቃት እንደማታደርስ ማስተማመኛ እስካልተገኘ ድረስ አልመለስም ስትል ቆይታለች፡፡
በተመድ እና በቱርክ አሸማጋይነት ዩክሬን በጥቁር ባህር ላይ ዳግም ጥቃት እንደማትከፍት እና የጥቃት ኢላማ እንደማታደርግ ማስተማመኛ መስጠቷን የሩሲያ መከላከያ ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡
ዩክሬን በጥቁር ባህር ላይ ጥቃት እንደማትከፍት የማረጋገጫ ደብዳቤ ጽፋ ለሩሲያ መስጠቷን ያሳወቀው የሩሲያ መከላከያ ሚኒስቴር ሞስኮም አቋርጣው ወደ ነበረው የጥቁር ባር የስንዴ ማጓጓዝ ስምመነት መመለሷን አስታውቃለች ሲል ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
በዚህ ስምመነት መሰረት የዩክሬን ስንዴ እና ሌሎች የግብርና ምርቶች በጥቁር ባህር አድርገው ወደ ተቀረው ዓለም ያለምንም ገደብ እንዲጓጓዝ ሩሲያ እንደምትሰራም አስታውቃለች ተብሏል፡፡
የሩሲያ ፕሬዝዳንት ፑቲን ከዚህ በፊት እንደተናገሩት ከዩክሬን ተነስቶ በጥቁር ባህር አድርጎ ከሚጓጓዘው ስንዴ ውስጥ አብዛኛው ወደ አውሮፓ ሀገራት መጓጓዙን መተቸታቸው ይታወሳል፡፡