ከዩክሬን ወደ ኢትዮጵያ ሲጓጓዝ የነበረው ስንዴ መድረሱን የአለም የምግብ ፕሮግራም አስታወቀ
በሩሲያና ዩክሬን በተደረሰው “የእህል ስምምነት” መሰረት እህል ወደ ተለያዩ ሀገራት በመጓጓዝ ላይ መሆኑ ይታወቃል
ወደ ኢትዮጵያ የመጣው እህል በድርቅና በግጭት ለተፈናቀሉ ከ1 ነጥብ 5 ሚሊዮን በላይ ዜጎች በእርዳታ መልክ የሚሰጥ ነው ተብሏል
የዩክሬን የመሰረተ ልማት ሚኒስትር ኦሌክሳንደር ኩብራኮቭ በቅርቡ በትዊተር ገጻቸው ባጋሩት ጽሁፍ “ብሬቭ ኮማንደር” በተባለችው መርከብ አማካኝነት ከዩክሬን የተጫነው የእህል እርዳታ ወደ ኢትዮጵያ እንደሚጓጓዝ ገልጸው ነበር፡፡
መርከቧ 23 ሺህ ቶን ስንዴ ትጭናለች ተብሎ እንደሚጠበቅም ነበር ሚኒስትሩ በወቅቱ የገለጹት፡፡
የዓለም የምግብ ፕሮግራም (ደብሊውኤፍፒ) በጥቁር ባህር ላይ ከሚገኘው ፒቭዴኒ ከተባለ ወደብ መነሻው ያደረገው የእህል እርዳታ ጁቡቲ ወደብ ላይ ከተራገፈ በኋላ ወደ ኢትዮጵያ ዋናው መጋዘን መድረሱ አስታውቋል፡፡
እህሉ በድርቅና በግጭት ለተፈናቀሉ ከ1 ነጥብ 5 ሚሊዮን በላይ ዜጎች በእርዳታ መልክ የሚሰጥ ነው ተብሏል፡፡
በተባበሩት መንግስታት ድርጅት እና በቱርክ አደራዳሪነት ምክንያት ዩክሬን ከወደቦቿ እህል ወደ ሌሎች ሀገራት እንድታጓጉዝ ከሩሲያ ጋር ከስምምነት መደረሱ ይታወሳል።
ስምምነቱን ተከትሎም ከቅርብ ቀናት ወዲህ በርካታ የጭነት መርከቦች የተለያየ መጠን ያለው እህል ከዩክሬን ወደቦች ላይ ጭነው መንቀሳቀሳቸው ይታወቃል።