አውሮፓ ህብረቱ ቦሬል በአክራሪ የእስራኤል ሚኒስትሮች ላይ ማዕቀብ እንዲጣል ጠየቁ
የህብረቱ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ሃላፊው የእስራኤል የብሄራዊ ደህንነት እና የፋይናንስ ሚኒስትሮች ላይ ትችት ሲያሰሙ መቆየታቸው ይታወቃል
በብራሰልስ የተሰበሰቡት የህብረቱ አባል ሀገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች በቦሬል በቀረበው ጥያቄ ላይ ድምጽ እንደሚሰጡ ይጠበቃል
የአውሮፓ ህብረት የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ሃላፊው ጆሴፍ ቦሬል በአክራሪ የእስራኤል ሚኒስትሮች ላይ ማዕቀብ እንዲጣል ጠየቁ።
ሃላፊው በብራሰልስ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ ስማቸውን ያልጠቀሷቸው የእስራኤል ሚኒስትሮች በፍልስጤማውያን ላይ ያነጣጠሩ የጥላቻ መልዕክቶችን እያስተጋቡ ነው ብለዋል።
ሚኒስትሮቹ አለማቀፉን ህግ የጣሰና የጦር ወንጀል እንዲፈጸም የሚቀሰቅስ ንግግር ማድረጋቸውን በመጥቀስም ህብረቱ ማዕቀብ እንዲጥልባቸው ጠይቀዋል ብሏል ዩሮ ኒውስ በዘገባው።
ቦሬል ማዕቀብ እንዲጣልባቸው የጠየቁት በየትኞቹ የእስራኤል ሚኒስትሮች ላይ እንደሆነ በመግለጫው ባይጠቅሱም በቅርቡ የእስራኤል የብሄራዊ ደህንነት ሚኒስትሩን ኢታማር ቤን ግቪር እና የፋይናንስ ሚኒስትሩን ቤዛለል ስሞትሪች መተቸታቸው ይታወሳል።
ኢታማር ቤን ግቪር በአል አቅሳ መስጂድ ጉብኝት አድርገው በስፍራው የአይሁዳውያን ማምለኪያ እገነባለሁ የሚል አስተያየት መስጠታቸው አለማቀፍ ነቀፌታ አስከትሎባቸዋል።
እስራኤል በዌስትባንክ ህገወጥ የሰፈራ ቤቶችን መገንባቷን የሚቃወሙትን ሲወርፉ የቆዩት የፋይናንስ ሚኒስትሩ ቤዛለል ስሞትሪችም በጋዛ 2 ሚሊየን ፍልስጤማውያንን ማስራብ “ሞራል” ሊሆን ይችላል ሲሉ መሳለቃቸውን ተከትሎ ጆሴፍ ቦሬል በኤክስ ገጻቸው ላይ ተቃውሟቸውን አቅርበው ነበር።
27 አባል ሀገራት ያለው የአውሮፓ ህብረት ጆሴፍ ቦሬል ያቀረቡትን የማዕቀብ ጥያቄ ያጸድቀዋል ተብሎ ባይጠበቅም በእስራኤል ላይ የተጀመረውን ጫና እንደሚያጠናክረው ታምኖበታል።
የአውሮፓ ህብረት በሚያዚያ ወር እስራኤላውያን ሰፋሪዎች በዌስትባንክ እና ምስራቅ እየሩሳሌም በፍልስጤማውያን ላይ ጥቃት ማድረሳቸውን ተከትሎ ሁከቱን የመሩ አራት ግለሰቦችና ሁለት ተቋማት ላይ ማዕቀብ መጣሉ ይታወሳል።
በአሁኑ በቦሬል የማዕቀብ ጥያቄ ዙሪያ ድጋፍ የሰጠችው ብቸኛዋ ሀገር አየርላንድ ናት ተብሏል።
“ጆሴፍ ቦሬል በዌስትባንክ የሚካሄድ ህገወጥ ሰፈራን በሚያበረታቱና ሁከት በሚቀሰቅሱ አካላት እንዲሁም የጥላቻ መልዕክት ማስተላለፋቸውን በቀጠሉ ሁለት የእስራኤል ሚኒስትሮች ላይ ማዕቀብ እንዲጣል ያቀረቡትን ሃሳብ እንደግፋለን” ብለዋል የሀገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማይክል ማርቲን።
የጣሊያን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒዮ ታጃኒ ግን “ለፍልስጤማውያን በሃሳብ ደረጃ እውቅና መስጠትም ሆነ በእስራኤል ሚኒስትሮች ላይ ማዕቀብ በመጣል ችግሩ አይፈታም” በማለት የአውሮፓ ህብረት የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ሃላፊውን ምክረሃሳብ ውድቅ አድርገውታል።
በብራሰልስ ምክክራቸውን የጀመሩት የህብረቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች በጉዳዩ ላይ የሚሰጡት ድምጽ ይጠበቃል።